Fana: At a Speed of Life!

የጋሸና ላሊበላ ሰቆጣ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 204 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጋሸና ላሊበላ ሰቆጣ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለፀ።

የጋሸና ላሊበላ ሰቆጣ መንገድ አካል የሆነው የጋሸና ብልብላ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ከአጠቃላይ 105 ኪሎ ሜትር ውስጥ አሁን ላይ ግንባታው 87 በመቶ መድረሱ ተገልጿል፡፡

የመንገዱ 78 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ስራው መከናወኑንም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።

ለግንባታው 1 ነጥብ 87 ቢሊየን ብር ወጪ የሚደረግ ሲሆን ግንባታውን ዓለም አቀፉ የቻይና ሬል ዌይ ኢንጅነሪንግ ቁጥር 3 የስራ ተቋራጭ ያከናውነዋል።

የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ኢንጂነር ዘውዴ እና ዋይ ኤል ኤስ ኢንጂነሪንግ አማካሪ ድርጅቶች በጣምራ እያከናወኑት ይገኛል።

በተያያዘም ከፕሮጀክቱ 99 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የፕሮጀክቱ ቀጣይ ክፍል የሆነው የብልብላ-ሰቆጣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከአጠቃላይ የግንባታ ስራው ውስጥ 80 በመቶ ተጠናቋል ተብሏል።

ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውን የመንገድ ግንባታ ቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮ ሊሚትድ የተባለ የቻይና ዓለም አቀፍ የሥራ ተቋራጭ ድርጅት እያከናወነው ይገኛል፡፡

የጋሸና ላሊበላ ሰቆጣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ቀሪዎቹን ስራዎች በተያዘው በጀት ዓመት በተገቢው የጥራት ደረጃና ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.