Fana: At a Speed of Life!

የግብርናው ዘርፍ ከማምረቻ ኢንዲስትሪ፣ ወጪ ንግድ እና ከዜጎች እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት ሰፊ ስራ ይጠበቅበታል አቶ ዑመር ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴር ከክልል ግብርና ቢሮዎች ጋር በተጠናቀቀው በጀት አመት አፈፃፀም እና የ2015 እቅድ ላይ ውይይት እያደረገ ነው።

መድረኩን የከፈቱት የኢፌዴሪ የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን፥ ባለፈው በጀት አመት የነበረው አፈፃፀም መልካም ውጤቶች የተመዘገቡበት ቢሆንም፥ ዘርፉ በኢንደስትሪ በቤተሰብ ምግብ እና በወጪ ንግድ እያደገ የመጣውን ፍላጎት ለመመለስ በ2015 በጀት አመት ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅበት ነው የተናገሩት።

አቶ ዑመር፥ በበጋ መስኖ ስራ በተለይ በስንዴና በአበባ እርሻ ፣ በመኸር ምርት የእቅዱን 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል።

በ2014 በወጪ ንግድ ከተገኘው ገቢ ቡና ቀዳሚውን ሥፍራ መያዙን ሚኒስትሩ አንስተዋል።

በአበባ፣ አትክልት እና ፍራፍሬ፣ በስጋ ምርትም የተሻሉ ውጤቶች መገኘታቸውንም ያነሱ ሲሆን፥ በዚህ ዘርፍ ቀጣይ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይጠበቅበታልም ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ከታቀደው 374 ሚሊየን ኩንታል የመኸር ምርት 336 ሚሊየን ኩንታል ተገኝቷልም ነው ያሉት ሚንስትሩ።

በሜካናይዜሽን ዘርፍም ቀደም ሲል በተወሰኑ ክልሎች ብቻ ተወስኖ የነበረውን ወደ ሁሉም ክልሎች የማዳረስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ውይይቱ ዛሬም ቀጥሎ በክልሎች የተመረጡ ፈተናዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የ2014 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና ቀጣይ እቅድ ላይ ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በፀጋዬ ወንድወሰን

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.