Fana: At a Speed of Life!

የግብርና ምርቶችን ከማዕከላዊ ገበያ ጋር ለማገናኘት የሚያስችለው የአሊ ከተማ-ዋቤ ድልድይ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 56 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአሊ ከተማ-ዋቤ ድልድይ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ በጥሩ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ገለጸ፡፡

ፕሮጀክቱ በቅርቡ የአስፋልት ማንጠፍ ሥራ የጀመረ ሲሆን ፥ በአሁኑ ወቅት የ8 ኪሎ ሜትር አስፋልት የማንጠፍ ሥራ መከናወኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪ የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት ሥራ፣ የውሃ መፋሰሻ ቱቦዎች ሥራ፣ እንዲሁም የሰብቤዝ እና ቤዝኮርስ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡

የሶስት ድልድዮች ግንባታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲሆን ፥ የአንድ ድልድይ ግንባታ በቅርቡ ይጠናቀቃል መባሉን ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተደረገው የመስክ ቅኝትም ፕሮጀክቱ አሁናዊ አፈፃፀሙ ከ79 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን ፥ ይህም ከእቅዱ ጋር በሚጣጣም መልኩ እየተከናወነ መሆኑ ተገምግሟል።

ቀሪ የግንባታ ሥራውን አከናውኖ በሚቀጥለው በጀት ዓመት አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ነው የተገለፀው፡፡

ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ዓለም-አቀፉ የሥራ ተቋራጭ ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ሲሆን ፥ የማማከር እና የቁጥጥር ሥራውን ሆንግ አይኬ ከልደት ኮንሰልቲንግ ኢንጂነርስ ጋር በጥምረት እየሰሩ ይገኛል፡፡

ለግንባታው የሚውለው 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፥ ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ 427 ኪሎ ሜትር ርቀት አሊ ከተማ ላይ ጀምሮ ዋቤ ከተማ ላይ ያበቃል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ በአካባቢው በስፋት የሚመረተውን ስንዴ፣ ገብስ እና የፍራፍሬ ምርቶችን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶችን በስፋት እና በጥራት ወደ ማዕከላዊ ገበያ በማድረስ የአርሶ-አደሩን ተጠቃሚነት ይበልጥ እንደሚጨምር እንዲሁም የሶፍ ዑመር ዋሻ ፣የሳነቴ ተራራ እና የዲንሾ ብሔራዊ ፓርክ ለጎብኝዎች ምቹ በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለውም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.