Fana: At a Speed of Life!

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የግብጽ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር መግለጻቸው ጥሩ ጅማሮ እና የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፍ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡

አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሚ ሹክሪ ገለጻ ግብጽ በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ ቀደም ሲል ታራምድ የነበረውን አቋም በመቀየር ኢትዮጵያ የምታራምደውን አቋም ወደሚደግፍ ሃሳብ መሸጋገሯን የሚያመላክት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቃል አቀባዩ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዑጋንዳው ፕሬዚዳንት በአለ ሲመት ላይ በተገኙበት ወቅት፥ ከተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ጋር በጋራ እና ወቅታዊ በሆኑ ገዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጻዋል።

እንዲሁም በፈረንሳይ በተዘጋጀው በአፍሪካ የኮቪድ19 መከላከል በተለይም አፍሪካን ለመርዳት ፈረንሳይ በጠራችው ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከተለያዩ መሪዎች ጋር በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት፡፡

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የስራ ሀላፊ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

ቀይ መስቀል በኢትዮጵያ የሚመድበውን በጀት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለው ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጹንም ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ድርጅቱ ከሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋ ጋር በተያያዘ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የበለጠ ፍላጎት እንዳለው መግለጹንም ነው ያነሱት።

ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘም ምርጫውን ለመታዘብ ከዚህ ቀደም ከአሜሪካ ፣ ሩሲያ እና የአውሮፓ ህብረት ለሚመጡ ልዑኮች ፈቃድ መሰጠቱን አስታውሰው፥ ምርጫው መካሄድ የለበትም ከሚለው ሀሳብ ወጥተው በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ምርጫውን እንታዘብ የሚሉ ጥያቄዎች ማቅረብ መጀመራቸውን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ምርጫውን ለመታዘብ ከሀገር ውስጥ 36 የሲቪክ ማህበራት ፈቃድ አግኝተው ዝግጅት እያደረጉ ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የውስጥ ጉዳይ ላይ በተለያየ መልኩ ጣልቃ ገብነት እየተደረገ መሆኑንም አውስተዋል።

አምባሳደሩ እንዳሉት ጫናዎቹና ጣልቃ ገብነቶቹ በተለያየ ጊዜ መልካቸውን እየቀያየሩ የሚደረጉ ናቸው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን የውሀ ሙሌት አታካሂድም በሚል የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉ መቆየታቸውንና አሁን ላይ ጫናዎቹ እየቀነሱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በትግራይ ክልል ከተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘም በመንግስት በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን እውቅና ባለመስጠት ጫናዎች እና ጣልቃ ገብነቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጅ ይህ ጫና እና ጣልቃ ገብነት አግባብነትም ሆነ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡

በማህሌት ተክለብርሃን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.