Fana: At a Speed of Life!

የጎርፍ አደጋን ለመቅረፍ በተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል – አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመቅረፍ በተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎርፍ በተጎዱ አካባቢዎች ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግም መመሪያ ሰጥተዋል።

ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሃገራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ዛሬ ውይይት አካሂዷል።

በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ግድቦችና ወንዞች ከፍተኛ የውሃ መጠን መያዛቸው ተገልጿል።

በአዋሽ፣ ኦሞና አባይ ተፋሰሶች የሚኖሩ ዜጎች በዚሁ ምክንያት ለጎርፍ አደጋ መጋለጣቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ አስቀድሞ በተደረገ የመከላከል ስራ ሊደርስ የነበረውን አደጋ መቀነስ ተችሏል ተብሏል።

የምክር ቤቱ አባላት በውይይቱ ወቅት የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት መከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት መሰራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ሃገራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ተፈጥሯዊ አደጋዎች መከሰት አይቀሬ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ጉዳቱን እንዴት እንከላከል የሚለው ጉዳይ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ መሆን ይገባዋልም ነው ያሉት።

ከዚህ አንጻር የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው የተፋሰስ ልማት ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት መሆኑንም አስረድተዋል።

በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ከመደገፍ ጎን ለጎን በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን ማቋቋም እንደሚገባ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ችግሩ ከተከሰተ በኋላ አደጋውን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎች ካላቸው የአየር ጠባይ አንጻር ተላላፊ በሽታዎች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ ጥንቃቄ እንዲደረግም ነው ያሳሰቡት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.