Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ መንግስት በህወሓት ውስጥ የሚገኝ ጽንፈኛ ቡድን ህገ መንግስቱን በመጣሱ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራን ለመስራት መገደዱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ፥ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የህወሓት አጥፊ ቡድን በትግራይ በሚገኘው የሰሜን እዝ በሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ መንግስት በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቅፅ 51 በተሰጠው ስልጣን መሰረት መጠነ ሰፊ የህግ ማስከበር ኦፕሬሽን  እያካሄደ መሆኑን ገልጿል።

ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት በኃይል ሲመራ የነበረው የህወሓት ቡድን አሁን በስልጣን ላይ ያለው የኢፌዴሪ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ከህግ ተጠያቂነት በመሸሽ በመቐለ ከተማ ራሱን ህዝብ ውስጥ ሸሽጎ ይገኛል ብሏል።

የህወሓት አጥፊ ቡድን ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ሲፈጥር መቆየቱን በመግለፅ፤ መንግስት ከህወሓት ጋር ያለውን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ለወራት ታግሶ ድርድርና ሽምግልና ሲያካሂድ መቆየቱንም አስታውሷል።

ሆኖም ግን ወንጀለኛው ህወሓት ቡድን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሀገሪቱን ችግር ውስጥ ለማስገባት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በምእራብ ጎንደር፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በቡኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በጉረ ፈርዳ እንዲሁም በቅርቡ በምእራብ ወለጋ በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ጀርባ እንዳለም መግለጫው አመላክቷል።

የፌደራሉ መንግስት ገለልተኛ አደራዳሪዎችንም ጭምር በመጠቀም ልዩነቱን ለመፍታት ያደረገውን ጥረት ወደ ጎን ያለው ህወሓት አጥፊ ቡድን ይባስ ብሎ በክልሉ ህገ ወጥ ምርጫ በማካሄድ ራሳቸውን ህጋዊ መንግስት ነን ሲሉ መቆየታቸውንም አስታውሷል።

ከዚህም በማለፍ የህወሓት አጥፊ ቡድን የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ ከ20 ዓመታት በላይ በትግራይ መቀመጫውን ያደረገውን የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ ድንገተኛ ጥቃት መክፈቱን በማስታወስ፤ ሰራዊቱም ራሱን እንዲከላከል እና የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ማድረግም የፌደራል መንግስት ያደረገው ብቸኛ ተግባርም ነው ብሏል።

ይህንን ተከትሎም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ለ6 ወራት ተፈጻሚ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣቱን እና የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም አዋጁን ማጽደቁን አስታውሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ግብረ ኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።

ግብረ ሀይሉ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜም፦

  • ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውንም የፀጥታ ሃይል ትጥቅ እንዲፈቱ ማድረግ
  • የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ጨምሮ አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መጣል
  • የሰአት እላፊ ገደብ የማውጣት
  • የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴዎችን የማስቆም
  • የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ የማድረግ
  • ህገ ወጥ በሆነ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች የመያዝና የማቆየት ኃላፊነት ይኖረዋል።

የፌደራል መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ ህገ መንግስቱን የመጠበቅ እና መከላከል እንዲሁም የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንደሚወጣም መግለጫው አስታውቋል።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም በትግራይ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የእነዚህን ወንጀለኞች ቡድን ተግባር ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚያስቆሙም በመግለጫው ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.