Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሁሉም በየቦታው ለኢትዮጵያ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ሁሉም በየቦታው 24 ሰዓት ለኢትዮጵያ ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቀረበ፡፡

ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ታምና በሕዝቧ አንድነትና ጽናት የቆመች ሀገር ና፤ ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዟት በሚሞክሩ ተማምና አታውቅም፤ ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ።

ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ነው፤ የገነቧት ደግሞ ልጆቿ ናቸው። እነዚህ ልጆቿ በከፈሉት መሥዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን ሠርታለች። እነዚህን አስደናቂ ታሪኮች ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት፤ የከዷት ወዳጆችም ነበሩ፤ ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም።

ነገር ግን የዓለም ታሪክ ያረጋገጣቸው ሁለት ሐቆች አሉ፤ ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም የሚለው ቀዳሚው ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርም የሚለው ደግሞ ሁለተኛው።

የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ ነው፤ ኢትዮጵያውያን፣ አሰቡት፤ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፤ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ይጨርሱታል፤አይቀሬ ነው።

የሚያዋጣን ኅብረት አንድነታችን ነው፤ ለእኛ ያለነው እኛ መሆናችንን አውቀን ስለ እኛ ጉዳይ እኛው ራሳችን ኢትዮጵያን አለንሽ እንበላት፡፡
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነን ለኢትዮጵያ እንቁም፤ ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም፤ ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው።

ማንም ገዝቶን አያውቅም፤ ወደፊትም ማንም አይገዛንም፤ ታሪክ የሠሩ እጆች ዛሬም አሉ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ወዳጆቻቸውን ለማክበር እንጂ ጠላቶቻቸውን ለመታዘዝ ተንበርክከው አያውቁም። ዛሬም ወደፊትም አናደርገውም።

ክንዳችንን እናበርታ። ትከሻችንን እናስፋ። ልባችንንም እናጽና። ከውጭና ከውስጥ የተሠነዘረብንን ጥቃት ድል አድርገን መሻገር ብርቃችን እንዳልሆነ እናስመስክር።

በምንምና በማንም ካሰብነው መንገድ እንቀርም። ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል የለም። አንድ ሆነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ ነው። ዛሬም ያንን ጋሻ በአንድነት እናንሣ። ሁላችንም፣ በየቦታችን፣ 24 ሰዓት፣ ለኢትዮጵያ እንቁም።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.