Fana: At a Speed of Life!

የጠ/ሚ ዐቢይ ጦሩን በግንባር መምራት የአባቶቻችን ጀግንነት እና የሀገር ፍቅር ስሜት ቀጣይነት ማሳያ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጦሩን በግንባር መምራት የአባቶቻችንን ጀግንነት እና ከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ቀጣይነት እንዳለው ያረጋገጠ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ገለጹ፡፡
 
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮናስ ዘውዴ እና የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ግንባር መዝመት ከሰራዊቱ ባለፈ በሌሎች ዜጎች ላይ የፈጠረው መነቃቃት ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 
አቶ ዮናስ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ መሪዎች ሀገራቸው የህልውና አደጋ የሚገዳደር ወራሪ ሲገጥማት መሪዎች ቤተመንግስት ከመቀመጥ ይልቅ ድንኳኖቻቸውን ይዘው ጦሩን እየመሩ ከቦታ ቦታ አብረው ይዘዋወሩ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
 
አሁን በእኛ ዘመንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንኑ ደግመውታል ነው ያሉት ሃላፊው፡፡
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን ከፍ ሲልም ዓለምን ያነቃቃ ነው ያሉት አቶ ዮናስ÷ ሀገራቸውን ለመምራት ብቻ ሳይሆን ለሀገራቸው ለመሰዋትም ዝግጁ መሆናቸውን ያሳዩበት እና ሀገር ከምንም እንደሚበልጥ ትምህርት የሰጡበት መሆኑን አውስተዋል፡፡
 
ጦርነቱን በድል ከማጠናቀቅ ጎን ለጎንም በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ፣ በኮሙኒኬሽን እና በሌሎች ዘርፎች ስኬትን ለማስመዝገብ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
 
የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ በበኩላቸው ÷ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የተሰለፉ ኃይላት በኢኮኖሚ ጡንቻቸው የፈረጠመ፣ በሚዲያ ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉ፣ የዓለምን የፖለቲካ ሚዛን ሲዘውሩ የነበሩ እና ከዚህ በፊትም ሌሎች ሀገራትን በሤራ ያፈረሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
 
ስለሆነም የእነዚህን ኃይሎች ተፅዕኖ በድል ለመወጣት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት እና ለሠራዊቱ የቅርብ አመራር መስጠት ሚናው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
 
ሁኔታው የውክልና ጦርነት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጦርነቱን በድል ለመወጣት በተደረገው ጥረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፊት ሆነው በመምራታቸው አመርቂ ድሎች የተገኙበት እና ምዕራባዊያን እንዳሰቡት የጠላት ኃይል ወደ አዲስ አበባ ሳይሆን ወደ መቀሌ እግሬ አውጭኝ ብሎ እየፈረጠጠ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
 
በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ሲቋምጡ የነበሩት ምዕራባዊያንም ፣ የነሱ ጣልቃ ገብነት ከኢትዮጵያውያን በላይ ኃይል እንደሌለው ግንዛቤ የወሰዱበት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
 
አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.