Fana: At a Speed of Life!

የጤና ሚኒስቴር እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ጋር ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስቴር እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድ ጋር ተፈራረሙ፡፡

ስምምነቱ በጤናው ዘርፍ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎችን ለማቅረብና ቀጣሪዎችን ከሥራ ፈላጊ የጤና ባለሙያዎች ጋር የሚያገናኙ ዘመናዊ ዘዴዎችን ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በፌስ ቡክ ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ሥራ እየፈለጉ ባሉበት እና እንዲሁም የሥራ ገበያው ፍላጎትና አቅርቦት ባለመጣጣማቸው የተለየ ትኩረት ተሰጥቶት የተጀመረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ተቋማቱ ተመራቂ የጤና ባለሙያዎች አመርቂ የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማመቻችት፣ ወጣት የጤና ባለሙያዎች የራሳቸውን የጤና አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ እንዲመሰርቱ ለማበረታታት፣ በዘርፉ ሥራ ፈጠራን ለማስፋፋት እንዲሁም በውጪ ሃገራት ያሉ ዕድሎችን ለመፈተሽ እና ለማስተዋወቅ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎችን ወደሥራ ለማሰማራትና ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት በሃገር ውስጥ ሥራ ማስያዝ፣ የውጭ ሀገራት የሥራ ዕድሎችንና አማራጮችን ማመቻቸት እንዲሁም አዳዲስ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴሎች ላይ መሰማራት እንዲችሉ የማመቻቸት ሥራዎች መለየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም በዋናነት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ከሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ሞዴሎችን እንዲፈቀዱ በማድረግ ለመተግበር እንዲቻል የተለያዩ ሃገራትን ልምድ በመቀመር የጤና ባለሞያዎች በተናጠልም ሆነ በጋራ የህክምና አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የሚያስችሉ መመሪያዎችን የማዘጋጀት ሥራ ተጠናቆ የቤት ውስጥ የጤና አገልግሎት እንዲሁም በስልክ ጥሪ የሚደረጉ የጤና ድጋፎች መመሪያ ክለሳ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው የሥራ ገበያው ላይ የሚታየውን የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን የማስተካከል ዕቅድን ለማሳካትና ተምረው የሥራ ዕድል ያላገኙ የጤና ባለሙያዎችን በተገቢው ደረጃ ሥራ ለማስያዝ በማንኛውም መንገድ ለመደገፍና ለማስተባበር ኮሚሽኑ ዝግጁ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከጤናው ዘርፍ ጋር የጀመረውን ትብብር ውጤታማ በማድረግ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ለመሥራትና የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ከሌሎች የመንግስት ተቋማትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር አዳዲስና ዘመናዊ አሠራሮችን በመዘርጋት በማስተዋወቅ የሥራ ገበያውን ጤናማ የማድረግ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ይህን ለመተግበርም ሥራ ፈላጊዎችን የሚመዘግብና በቴክኖሎጂ የሚደገፍ መተግበሪያ (National Recruitment Platform) አዘጋጅቶ በስራ ላይ ማዋሉን ጠቅሰው፥ መተግበሪያው ከሚያዝያ 18 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የሚውልና የቀጥታ (ኦንላይን) https://health-care.jccnrp.com/ አድራሻ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.