Fana: At a Speed of Life!

የጥቅምት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ አለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የጥቅምት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ19 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ ማለቱን ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው የጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም የምግብ ዋጋ ግሽበትም ካለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጋር ሲነጻጸር በ23 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል።

በጥቅምት ወር በአብዛኞቹ የእህል ዓይነቶች ላይ የታየው ጭማሪ ለምግብ ዋጋ ግሽበት ከፍተኛ ሚና እንደነበረው ኤጀንሲው አስታውቋል።

በዳቦ፣ እንጀራ፣ ስኳር፣ ከውጭ የሚገባ የምግብ ዘይት፣ ድንች፣ በርበሬ እና የቡና ዋጋ ላይ ጭማሪ መታየቱም ለዋጋ ግሽበት መጨመር ምክንያት መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።

በአንፃሩ በበቆሎ፣ ስንዴ፣ አትክልትና አንዳንድ የጥራጥሬ እህል ዓይነቶች ላይ መጠነኛ የዋጋ ቅናሽ መመዝገቡም ተገልጿል።

ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች የዋጋ ግሽበት የጥቅምት 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ14 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ኤጀንሲው ገልጿል።

በአልኮል፣ ትምባሆ፣ ጫት፣ የቤት ማፅጃ እና ኢነርጂ (የማገዶ ከሰል)፣ የቤት መስሪያ ቁሶች፣ የህክምና እና ጌጣገጥ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመኖሩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ግሽበት ከፍ እንዲል ማድረጉም ተመልክቷል፡፡

የጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው መስከረም ወር ጋር ሲነፃፀር በዜሮ ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.