Fana: At a Speed of Life!

የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰም ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ሆኗል -ዶ/ር ቢቂላ ሁሪሳ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 15፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጽንፈኝነትና አክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰም ለግጭቶች መከሰት መንስኤ ሆኗል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ብሄርን፣ ሃይማኖትን፣ ወሰንንና ሌሎች ማንነቶችን ሽፋን በማድረግ የተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ናቸው።

ግጭቶቹን ተከትሎም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ የግለሰብ፣ የህዝብና የመንግስት ንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።

የብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ÷ እነዚህ ግጭትች የውስጥና የውጪ ሀይሎች ተጣምረው የፈጠሯቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሕዝብ ግፊትና ጫና የመጣውን ለውጥ መቀበል የተሳናቸው አካላት ለውጡን ለማደናቀፍ ግጭቶችን ሲጠነስሱ፣ በገንዘብ ሲደግፉና ለጥፋት የመለመሏቸውን ሃይሎች ሲሰማሩ እንደነበረም አንስተዋል።

ጸረ ለውጥ ሃይሎች ከኢትዮጵያ ሕዝብ ያለአግባብ ያጋበሱትን ሀብት መልሶ ለማግኘትና ስልጣንን ዳግም ለመቆጣጠር ብዙ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታወሱት ዶ/ር ቢቂላ÷በኢትዮጵያ ያለውን ያልዳበረ የፖለቲካ ባህል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመውበታልም ብለዋል።

ከሁሉም በላይ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት ሲዘራ የነበረውን የጥላቻና በጥርጣሬ የመተያየት ትርክት ለግጭት መፍጠሪያነት ማዋላቸውን ገልጸው÷የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አስተሳሰብ አለመክሰሙ ግጭቶቹ እንዲባበሱ ካደረጉ ክስተቶች መካከል ዋነኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለውጡን ማደናቀፍ የሚፈልጉ አካላት አዝማሚያውን ለግጭት መፍጠሪያና ማባባሻነት ተጠቅመውበታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የራሷን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በራሷ አቅም የማትፈታ ደካማ አገር እንድትሆን ቀን ከሌሊት ሲሰሩ የነበሩ የውጭ አካላት መኖራቸውን አንስተዋል።

የውስጥና የውጭ ሃይሎች የተናበበ ሴራ ኢትዮጵያውያንን እንደ ሕዝብ የጎዳ መሆኑን ጠቅሰው÷ ንጹሓን ዜጎች መገደላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን እንዲሁም  ሃብት ንብረታቸው መውደሙን አስረድተዋ።

ነገር ግን ጸረ ለውጥ ሃይሉ እንዳሰበው ኢትዮጵያን ማፍረስ እንዳልቻለና ኢትዮጵያ በዜጎቿ መሰዋዕትነት የምትጠበቅ አገር መሆኗ ተረጋግጧል  ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.