Fana: At a Speed of Life!

የፈረንሳይ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ ይፈልጋሉ – አምባሳደር ሬሚ መርቻው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንደሚፈልጉ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ መርቻው ገለጹ።
አምባሳደር ሬሚ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ሥራ ተሰማርተው የሚገኙ የፈረንሳይ ኩባንያዎች 55 መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ኩባንያዎቹ በኃይል ዘርፍ በዋናነት በእንፋሎት እና ውኃ ኃይል ልማት እንዲሁም በማምረቻው ዘርፍ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም የፈረንሳይ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሎጂስቲክስ፣ በኃይል፣ በመጓጓዣ እና ቴሌኮም ዘርፍ የመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው ብለዋል።
ኤምባሲው በርካታ አልሚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በርካታ ዘዴዎችን እየተጠቀመ መሆኑንም አምባሳደር ሬሚ ጠቁመዋል።
ለአብነትም ‘የአፍሪካ ተልእኮ’ በሚል የሚዘጋጀው ሁነት በመጭው ኅዳር ወር እንደሚኖር ተናግረዋል።
ጥር ወር ላይ ደግሞ በዚሁ እንቅስቃሴ አማካኝነት ትልቁ የፈረንሳይ አልሚዎች ኅብረት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ በሁለቱ ሃገራት በኩል የመሪዎች ጉብኝት መካሄዱንና በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ መጠናከሩንም አመልክተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.