Fana: At a Speed of Life!

የፈረንጆቹ  2021 የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ተብሎ ተሰየመ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)  የአለም የጤና ድርጅት የፈረንጆቹን 2021  ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ብሎ  ሰይሟል።

ዛሬ በተባካሄደው መድረክም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመትን  በይፋ አስጀምራለች።

ይህ የስያሜ ዓመትም “መከላከል፣ ማልማት፣ እና አብሮነት”   በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገልጿል።

ይህም ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት እና የበጎአድራጎት ድርጅቶችን ለዘርፉ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት እንዲያሳድጉ፣ የጤና ባለሙያዎች ለኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው፣ ምቹ እና ራሳቸውን ከአደጋ ለመካለከል የሚያስችል የስራ ቦታ እንዲፈጠር እንዲሁም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከጤና ባለሙያዎች ጎን እንዲቆም የተግባቦት ስራዎች መስራት ላይ ያተኩራል ነው የተባለው።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ከ2019 ጀምሮ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተከትሎ የጤና ባለሙያዎች የከፈሉትን ከፍተኛ መስዋዕትነት እና ህብረተሰቡን ለማገልገል ያሳዩትን ከፍተኛ ጥረት በማሰብ ተገቢውን ምስጋና እና እውቅና ለመስጠት 2021 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመት ሆኖ ተሰይሟል ብለዋል።

በኢትዮጵያም የጤና ባለሙያዎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እና ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት ላይ ግንባር ቀደም የሆነ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል  ብለዋል።

በዚህም ወቅት ለኮቪድ 19 በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ከመሆናቸው አንጻር ተገቢውን  ራስን ከበሽታ መከላከያ ቁሳቁስ በማቅረብ፣ በኮቪድ 19 ዙሪያ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ለኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ እና ሌሎች ተመሳሳይ ስራዎች ሲሰሩ  መቆየታቸውን ዶክተር ሊያ ተናግረዋል ።

ህብረተሰቡም ከቫይረሱ እራሱን በመጠበቅ በባለሙያዎቹ ላይ ያለውን ጫና በመቀነስ ወረርሽኙ ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ አለበት ሲሉ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

በመድረኩም ላይ ዓለም አቀፍ የጤና እና ክብካቤ ባለሙያዎች ዓመትን በይፋ ከማስጀመር በተጨማሪ በኢትዮጵያ  የሚስተዋለውን የጤናው ዘርፍ የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ውልም የጤና ሚኒስቴር እና የተለያዩ የጤና ሙያ ማህበራት መፈራረማቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.