Fana: At a Speed of Life!

የፋናን 25ኛ አመት ምክንያት በማድረግ የአፋን ኦሮሞ የስርጭት ጊዜ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 21 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባለፉት 25 ዓመታት የአፋን ኦሮሞ የስርጭት ጊዜ ላይ የሚያተኩር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው፥ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የዛሬ 25 አመት በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ሰፊ ሰዓት በመስጠት የመጀመሪያው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ከዋናው ጣቢያ የስርጭት ሰዓት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል አምስት የኤፍ ኤም ጣቢያዎች በመክፈት ለህዝቡ ይበልጥ ተደራሽ መሆን መቻሉንም አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ባለፋት 25 ዓመታት የኦሮሞ ቋንቋ፣ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ታሪክ እንዲጎለብት አይነተኛ ሚና ተጫውቷልም ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የፌደራል የፍትህና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር እና የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የቦርድ አባል አምባሳደር ደግፌ ቡላ በበኩላቸው፥ ፋና የሀገሪቱ ህዝቦች ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ፣ ዘመናዊ አኗኗርን እንዲከተሉ እንዲሁም ልማት እና ዴሞክራሲ እንዲሠፍን ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

በመድረኩ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ምሁራን ተገኝተዋል፡፡

በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በ25 ዓመታት ጉዞው የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ስርጭቱ በቋንቋ፣ ባህል አና ስነ ጥበብ እድገት እንዲሁም ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያበረከተው አስተዋጽኦ ላይ የሚያተኩር ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡

ፋና በቀጣይ ጊዜያት በዘርፉ የተሻለ ስራዎችን ይዞ በመቅረብ እና የአድማጭ ተመልካቾችን ፍላጎት ለማርካት በሚወስዳቸው የማሻሻያ እርምጃዎች ሊተኮርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችም በጥናታዊ ጽሁፉ ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

በማርታ ጌታቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.