Fana: At a Speed of Life!

የፋና ሥልጠና ማዕከል የእውቅና ፈቃድ አገኘ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ የስልጠና ማዕከል ስልጠናዎች እንዲሰጥ ከከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ አገኘ።
የስልጠና ማዕከሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት የጋዜጠኝነት እና የኮሙዩኒኬሽን ስልጠናዎችን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
ለፋና የስልጠና ማዕከል የስልጠና ፈቃዱን የሰጠው ተቋም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት፣ የሙያ ብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ባለስልጣን ነው።
የዕውቅና ፈቃድ ሰርተፊኬቱን የባለስልጣኑ የትምህርትና ስልጠና ተቋማት እውቅና ፈቃድና እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ የአይኔ አበባ ሰርጉ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተገኝተው ለኮርፖሬቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው አስረክበዋል።
ወይዘሮ የአይኔ አበባ በሰርተፊኬት ማስረከብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ፋና ይህንን የስልጠና ማዕከል ማቋቋሙ ለሀገራችን የሚዲያ ኢንዱስትሪ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቁመው ማዕከሉ ውጤታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው÷ ስልጠና ማዕከሉን ስንመሰርት ዓላማችን የሚዲያ ሙያ በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ እንዲሆን የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ በመሆኑይህን የዕውቅና ፈቃድ በማግኘታችን ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ መሰረት ይጥልልናል ብለዋል።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ሌሎች ተቋማትም አብረው እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ሥልጠናዎቹ በጋዜጠኝነት ሙያ፣ በሚዲያ ቴክኖሎጂ፣ በኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት፣ በማርኬቲንግ፣ ፋይናንስ እና በአስተዳደራዊና ተዛማጅ የሙያ ዘርፎች ለተውጣጡ 19 የስልጠና መስኮች ላይ ነው።
የስልጠና ማዕከሉ የመሳሪያና የሰው ኃይል ዝግጅት፣ የካሪኩለም ቀረጻ፣ የአሰልጣኞች ምልመላ እና የስልጠና ቦታ የማመቻቸት ስራዎች መጠናቀቃቸውን የገለጹት የስልጠና ማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ኃይሌ ፥በቀጣይም ሰልጣኞችን ለመቀበል ሙሉ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
በሀበነዮም ሲሳይ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.