Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች እንደ አስፈላጊነቱና ተቋማቱ በሚያወጡት የአፈፃፀም ደንብ መሰረት ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮቪድ19 ሥርጭትን ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች እንደ አስፈላጊነቱና ተቋማቱ በሚያወጡት የአፈፃፀም ደንብ መሰረት ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ውሳኔ አሳለፈ።
 
ውሳኔው ተፈፃሚ የሚሆነው እያንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማን መደበኛ የስራ ገበታው ላይ እንደሚገኝ እና ማን ከቤት ስራውን መስራት እንደሚችል በመወሰን በሚያወጡት ደንብ መሰረት መሆኑንም አስታውቋል።
 
ምክር ቤቱ ይህንን ውሳኔ ያሳለፈውም በትራንስፖርት ላይ ያለውን ጫና እና በከተማዋ ያለውን ዝውውር ለመግታት በማሰብ እንደሆነም ነው የተመለከተው።
 
የምክር ቤቱ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
 
17ኛ አስቸኳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ዉሳኔዎች
 
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮቪድ19 ሥርጭት ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለመከላከል የሚወሰዱ ርምጃዎችን በተመለከተ 17ኛ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል።
 
በዚህ ስብሰባ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የኮቪድ19 ሥርጭትን ለመከላከል የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች ከነገ መጋቢት 16፣ 2012 አንሥቶ ተጨማሪ ውሳኔ እስከሚተላለፍ ድረስ ሥራቸውን በቤታቸው ሆነው እንዲያከናውኑ ወስኗል። ከቤታቸው ሆነው የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች በእያንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አማካኝነት በሚወጣ ደንብ የሚለዩ ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቹ ለሠራተኞቻቸው ማን ከቤት ሆኖ እንደሚሠራ የሚያስታውቁ ይሆናል።
 
በዚህ ወቅት፣ ከቤታቸው ሆነው የሚሠሩ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አስተዋጽዖዋቸውን ለሚፈልጉ ሥራዎች ዝግጁ እና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የሚወጡ መሆን ይኖርባቸዋል። ይህ ውሳኔ የተወሰነው፣ በመላው አዲስ አበባ የሚካሄድ እንቅስቃሴን እና የትራንስፖርት ዘርፉን መጨናነቅ ለመቀነስ ታስቦ ነው።
 
ከጤና፣ ከደኅንነት ዘርፍ እና ከኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴዎች በተጨማሪ፣ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት የኮቪድ19ን ወረርሽኝ ለመከላከል ተጨማሪ ንዑስ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። ከተጨማሪዎቹ ንዑስ ኮሚቴዎች ውስጥ የአግልሎ ማቆያ ኮሚቴ ይገኝበታል። አግልሎ የማቆያ ተቋማትን የማዘጋጀት እና አስፈላጊ ግብአቶችን የማሟላት ሥራን በበላይነትያስተባብራል። የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂው ንዑስ ኮሚቴ ደግሞ፣ ግንዛቤን ለማስጨበጥ፣ ከኮቪድ19 ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ለማስተባበርና የተግባቦት ሥራን ለማካሄድ እንዲሁም ለስብሰባዎች የሚሆኑ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለማመቻቸት ይሠራል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.