Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያሰለጠናቸውን የፀጥታ እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት አመራሮች እና አባላትን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 6፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ያሰለጠናቸውን የፀጥታ እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት አመራሮች እና አባላትን አስመርቋል።

ስልጠናው ለአዳዲስ እና ነባር አመራሮች እና አባላት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የፀጥታ እና ህግ ማስከበር ዳይሬክቶሬት የተሰጠ ነው።

በስልጠና ወቅት ዘመናዊ የአድማ ብተና ትምህርትን ጨምሮ የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር፣ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሳዊ አገልግሎት፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ እና የአካል ብቃት ስልጠናዎችን ወስደዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ከህዝብ የተሰጠንን አደራ በአግባቡ በመወጣት የፖሊስን ሃይል እየተፈታተኑ ያሉ ግጭቶችን ለመከላከል የተጀመሩ የስልጠና ሂደቶች አመላካች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናው ወታደራዊ ዝግጅትን፣ ፖሊሳዊ ስነ ምግባርን፣ የህዝብ አገልጋይነትን እና ወገንተኝነትን ያካተተ እና በህዝቡ ዘንድ ያለውን ስጋት ለመቅረፍ የሚያስችል ነው ተብሏል።

በሀገሪቱ በተጀመረው ለውጥ መላ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሰላም ማስፈን እና የህግ ማስከበር ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት መፈፀም ይገባዋል መባሉን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.