Fana: At a Speed of Life!

የፌደሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች ለሚሰጠው የድጎማ በጀትን ግልጽ አሰራር ለመዘርጋት ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የፌደሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች ለሚሰጠው የድጎማ በጀትን ግልጽ አሰራር ለመዘርጋት ጥናት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

ምክር ቤቱ አሁን ተግባራዊ ከተደረገው ጥቅል አላማ ካለው የድጎማ በጀት አሰራር በተጨማሪ የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ልዩ አላማ ያለው የድጎማ ስርአት ለማበጀት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

እያከናወነ ያለውንም የሪፎርም ተግባር ከፌደራል፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች ጋር የተወያየ ሲሆን፤ የሪፎርሙ አስፈላጊነት፣ ይዘት፣ አሁን ያለበት ደረጃና የሚጠበቁ ውጤቶች አንዲሁም ሌሎች በለውጡ የተካተቱ ጉዳዮች ላይ ለውይይት መነሻ ቀርቧል።

የውይይቱ ተሳተፊዎችም በስራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት የአሰራርና፣ የመረጃና የተጠያቂነት ክፍተት በስፋት እንደሚስተዋልበት አንስተዋል።

የሚበጀተው በጀት ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበት አሰራር እንዳልነበር ጠቅሰው ቀጣይ መታየት ያለበት ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ አሁን በስራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት መሰረት የሚያደርገው የክልሎችን የገቢ አቅምና በስምንት ዋና ዋና ዘርፎች የክልሎች የወጪ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።

መስፈርቶቹ የተቀመጡበት የመረጃ ጥራትና ግልጽነት የሚጎድለው እንደሆነ ያነሱት አፈ ጉባኤው፤ እስካሁን ሲዘጋጁ የነበሩ ቀመሮች ያሉባቸው መሰረታዊ ክፍተቶች በጥናቱ ይታያሉ ብለዋል።

የፌደራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠው የድጎማ በጀት ለተፈለገው አላማ መዋሉን ቁጥጥር የሚደረግበት አሰራር ይዘረጋልም ነው ያሉት።

አሁን ተግባራዊ ከተደረገው ጥቅል አላማ ካለው ድጎማ በተጨማሪ እያንዳንዱ ክልል ያለበትን ክፍተት በማየት የተመጣጠነ እድገት ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ልዩ አላማ ያለው የድጎማ ስርአት ለማበጀት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት እያካሄደ ያለው የሪፎርም ጥናት በሰው ሃይል፣ በአደረጃጀትና በሌሎችም ራሱን በማጠናከር የተሰጠውን አላማ በብቃት ለመፈጸም ያለመ ሲሆን በቀጣዮቹ ወራት ይጠናቀቃል መባሉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.