Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል መንግስቱ ህጋዊነት ከከሰረው ቡድን ቅዥት ሳይሆን ከህገ መንግስቱ እና ከኢትዮጵያ ህዝቦች የመነጨ ነው – ዶክተር ዓለሙ ስሜ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ የፌዴራል መንግስቱ ህጋዊነት ከከሰረው ቡድን ቅዥት ሳይሆን ከህገ መንግስቱ እና ከኢትዮጵያ ህዝቦች የመነጨ መሆኑን ገለጹ፡፡

ዶክተር አለሙ ስሜ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በኢትዮጵያ መስከረም 25ም ሆነ ከዚያ በኋላ ጠንካራ እና ህጋዊ መንግስት አለ ይኖራልም ብለዋል።

ዶክተር አለሙ ቀን እየቆጠረ አንዴ ከመስከረም 25 በኋላ ሌላ ጊዜ ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም የሚለው ቡድን ህጋዊ ስልጣን የሌለው የቡድን ምኞቱን የሚናገር ስብስብ ነው ብለዋል፡፡

ይህም ሀሳብ ተራ ቅዥት እና ምንም እርባና የሌለው የከሸፋ ሃሳብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የፌዴረሸን ምክር ቤት ህግ መንግስታዊ ትርጉም ሰጥቶበት ምርጫው መራዘሙን ያነሱት ዶክተር አለሙ÷ ይህንን ተከትሎም የፌዴራል እና ክልል መንግስታት ምርጫው እስከሚካሄድ ስልጣናቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ህገ መንግስታዊ ውሳኔ ማሳለፉንም ተናግረዋል።

የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግስታት ስልጣንም ህጋዊነትም ህገ መንግስታዊ ስልጣን ከተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ እና ከሀገሪቱ ህዝቦች እንጂ ህጋዊ ስልጣን ከሌለውና ከከሰረው ቡድን አይመነጭም ብለዋል ዶክተር አለሙ ስሜ።

ዶክተር አለሙ የሀገሪቱ ሰላም እና ጠንካራ መንግስት ባለቤትነት በመላ ኢትዮጵያውያን የሚፈለግ በመሆኑ ከመስከረም 30 በኋላ መንግስት የለም የሚለው የጨነገፈ ሃሳብ በስልጣን ከሰከረው እና በስልጣን እጦት ካበደው ቡድን በስተቀር ገዥም ሆነ ተቀባይ የለውምም ብለዋል።

ዶክተር አለሙ ስሜ መስከረም 25 እና መስከረም 30 የሚባሉ ቀናት መንግስት የለም በሚል ቅዥት ከሚንገላታው ቡድን በስተቀር፤ ለመንግስትም ሆነ ለመላው ህዝብ ከመስከረም ወር ቀናት መካከል ያሉ ሁለት መደበኛ ቀናት ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ህግ መንግስቱን መሰረት ካደረገ ምርጫ በስተቀር ሌላ ስልጣን መያዣ መንገድ እንደሌለ የተናገሩት ዶክተር አለሙ ስሜ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ግፍ ሲፈፅም የኖረው እና በህዝቡ የተተፋው አካል ቀን ቆጠራ ላይ የተመሰረተ ቅዥትም የከሸፈ ህልም ነው ብለዋል።

በብልፅግና የሚመራው መንግስት፤ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት፤ በሃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በዓላት ግጭት ለመፍጠር የሚወጠኑ ሴራዎችን ማክሸፉን እና ይህንን ሀገር እና ህዝብን የመጠበቅ ሃላፊነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዶክተር አለሙ ስሜ ተናግረዋል።

በተጨማሪም የመንግስት ዋና ትኩረት በተቻለ መጠን በፍጥነት ሀገራዊ ምርጫ በማካሄድ፤ ዜጎች በፈቃዳቸው በመረጡት መንግት እና መሪ የሚመርጡበትን እድል ማመቻቸት ነው ብለዋል።

ከምርጫ ውጭ የሆነ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ጉዞ ወደ ኋላ የሚያንሸራትት ኢ-ህገ መንግስታዊ አማራጭ፤ በመንግስትም ሆነ በኢትዮጵያ ህዝቦች በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ዶክተር አለሙ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.