Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት  ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 25 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ750 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ተመረቀ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር  ኢንጂነር አይሻ መሃመድ÷ አገራችን የፍትህ ስርዓትን ሙሉ በሆነ መልኩ ለማስፈን ብሎም የዳኝነት አገልግሎቱን ቅልጥፍና ለማሻሻል፣ ጥራቱን ለማሳደግና ነፃነቱንም ለማስጠበቅ ብሎም ዳኞች ሙሉ አቅማቸውን በዳኝነት ስራ ላይ እንዲያውሉ በማድረግ በኩል የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ያለው ትርጉም እጅግ ታላቅ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሯ  በአገራችን የመኖሪያ ቤት እጥረት የዜጎች ዋነኛ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው÷ ባለፉት ዓመታት በመንግስት አስተባባሪነትና ድጋፍ እጅግ በርካታ ለሆኑ ዜጎች የመኖሪያ ቤት ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት  የተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

ሆኖም ካለው እጅግ ከፍተኛ ፍላጎት ጋር ያልተጣጣመ በመሆኑ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጥያቄው ዛሬም አፋጣኝ ምላሽንና ትኩረትን የሚሻ  ነው ብለዋል።

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁትን  መኖሪያ ቤቶች የሚረከቡ የፌዴራል ዳኞች መንግስትና ህዝብ የጣለባችውን ከባድ ኃላፊነት በመወጣት በኩል የመኖሪያ ቤት ችግሩ በዚህ ደረጃ መቃለሉ የሚኖረው ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል።

አያይዘውም በቀጣይ የመንግስት ሠራተኞችን ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት ዕጥረት ለመፍታት የጀመርናቸውን ጥረቶች አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል ።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ቁልፉን የተረከቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው÷ ከአራት ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረው ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት ላይ በመዋሉ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

የግንባታ ስራው እንደሌሎች ግንባታዎች ሁሉ  ከፍተኛ  ውጣ  ውረድ  የነበረበት ቢሆንም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በሌሎች አካላት በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ የታለመለትን ግብ ሊመታ እንደቻለ ተናግረዋል።

በዳኝነት ሙያ ለተሰማሩ ሰዎች መኖሪያ ቤት ከመኖሪያ ቤትነት ባለፈ የስራ ቦታ በመሆኑ ለዳኞች ምቹ መኖሪያ ቤት መሰራቱ የዳኝነት ስርዓቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ ዳኞች ከህዝብ የሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ያደርጋል ብለዋልፕሬዝዳንቷ ።

የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተክለ ፃድቅ ተ/አረጋይ ÷ የፌዴራል መንግስት ህንጻዎች ግንባታ በዋናነት የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶችን የህንፃ ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አላማ አድርጎ የተቋቋመ ተቋም መሆኑን  ተናግረዋል።

በዚህም ጽህፈት ቤቱ  በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ከ33 በላይ የሚሆኑ ህንፃዎችን 20 ለሚሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ ጽህፈት ቤቱ በአሁኑ  ወቅት የ 14 ህንጻዎችን ግንባታ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ÷የፌዴራል ዳኞች የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ ከ 900 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ተይዞለት የተጀመረ ቢሆንም ከታሰበለት በታች 750 ሚሊየን ብር ባልበለጠ በጀት ለማጠናቀቅ እንደተቻለ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት 80 ቤቶች እንደተላለፉ የገለፁት ስራ አስኪያጁ ÷የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ግንባታ ፕሮጀክት በልዩ ልዩ ምክንያቶች መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ ዘግይቶ የተጠናቀቀ ቢሆንም ፕሮጀክቱ በጥራትና በበጀት አፈፃፀም በኩል በስኬት የተጠናቀቀ ነው  ብለዋል።

ፕሮጀክቱ  ከ12 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል  የፈጠረና ከዋናው ስራ ተቋራጭ በተጨማሪም 47 ንዑስ ስራ ተቋራጮችን  ማሳተፍ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

በመጨረሻም በመኖሪያ ቤቶቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን  ማሳረፋቸውን ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.