Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 550 ከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮችን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ኮሚሽኑ በአዋሽ 7 ፖሊስ ማሰልጠኛ ማዕከል ሲያሰለጥናቸው የቆየውን 550 የሁለተኛ ዙር የፀጥታና ህግ ማስከበር ከፍተኛና መካከለኛ የፖሊስ አመራሮችን አስመርቋል፡፡

ስልጠናው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅና ፖሊስ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደናቀፍ የሚጥሩትን ቀድሞ መከላከል እንዲችል አመራሮቹን ለማዘጋጀት እንደሆነ ተነግሯል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል መላኩ ፋንታ፥ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዳይካሄድ፣ ግድቡ እንዳይጠናቀቅ የውጭና የውስጥ ቅጥረኞች የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ በሚጥሩበት በዚህ ወቅት የአባቶቻችንን ታሪክ በትክክል በመረዳት ሀገራችንን በጀግንነት በመጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል አለብን ብለዋል።

በወንጀል መከላከል ዘርፍ የትምህርትና ስልጠና ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ከበደ ለገሰ በበኩላቸው፥ የስልጠና ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት የስልጠናው ዋና ዓላማ ተቋሙ የፖሊስ ሀይሉን በስልጠና በማብቃትና በእውቀትና በክሎት በማጎልበት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

በሀገራችን በቅርቡ የሚካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የአድማ ብተና አመራሮቹ ከወዲሁ ሙያዊ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በቂ ስልጠና ተሰጥቷቸዋልም ብለዋል፡፡

2ኛ ዙር ሰልጣኞች 54ሺህ ብር በማዋጣት በአዋሽ 7 አስተዳደር ለሚገኙ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው መቶ ሰዎች ማዕድ ማጋራታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የፖሊስ ዩኒቨርሲቲው የስልጠና ምክትል ፕሬዝዳንትና ምክትል ኮሚሽነር ጋሹ አለማየሁ፣ የፀረ-ሽብርና የተደራጁ ወንጀሎች ቁጥጥር ምክትል ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር አበራ ሁንዴ እንዲሁም ሌሎች የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮች፣ በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የስልጠና ዋና መምሪያ ህብረት የአዋሽ 7 ማሰልጠኛ ጥምር አካዳሚክ አመራሮች በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.