Fana: At a Speed of Life!

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ መጀመሩን ገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግ የተቀናጀ ሥራ መጀመሩን ገለፀ።

ኮሚሽኑ በዛሬው እለት ከሁሉም ክልሎች፣ ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር የቪዲዮ ኮንፈረንስ አካሄዷል።

በዚህም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለም በቪድዮ ኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው እስከ አሁን በተሰሩ ስራዎችና ባለው የምርጫ ሂደት ዙሪያ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

በምርጫ ዝግጅት ዙሪያ በፌዴራል ደረጃ በተዘጋጀ ዕቅድ መሠረት ሁሉም ክልል የራሱን ዕቅድ በማዘጋጀት በየደረጃው ላለው የፀጥታ መዋቅር ግንዛቤ ሰጥቶ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በየክልሉ ባለው የፀጥታ ሁኔታና ለምርጫው እንቅፋት ሊሆኑ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡

ከምርጫ ቁሳቁስ ስርጭት ጋር በተገናኘ የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች በጋራ በመቀናጀት በየምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ማድረስ እንዲቻልና ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር ከግብ እንዲደርስ መከናወን ባለባቸው ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ የጋራ ስራ እየሰሩ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

በተካሄደው በዚህ የጋራ ውይይት የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖችና ሶስት የክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በየክልላቸው ያለውን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ በስፋት አንስተዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ በየደረጃው ያለውን የግንኙነት ስርዓት በማጠናከርና የፀጥታ ስራውን በየ15 ቀን በመገምገም ሁሉም የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች ከፌዴራል ፖሊስና የራሳቸውም ቋሚ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የፀጥታ፣ የግብዓት አቅርቦት፣ የአቅም ግንባታ፣ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን፣ የጤና፣ የምርመራ እና የመረጃ ንዑስ ኮሚቴዎች በፌዴራል ፖሊስ ደረጃ እንደተደራጁት ሁሉ በሁሉም ክልልና በሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተዋቅረው ስራቸውን በቅንጅት መምራት እንዳለባቸውም ማሳሰባቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሁሉም የፖሊስ አባላት ግልጽ አረዳድ እንዲኖራቸው የአቅም ግንባታ ስልጠና በመውሰድ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የፀጥታ ስራ መስራት አለባቸው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ በመተንተን ና ቅድሚያ መሰጠት ያለበትን የምርጫ ክልልና ጣቢያ በመለየት እንዲሁም አስፈላጊውን የሰው ኃይል በአግባቡ በመጠቀም መሠራት አለበት ሲሉም ገልፀዋል፡፡

ፖሊስ የምርጫ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከወዲሁ ስርዓት የማስያዝ ስራ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ሰሞኑን የተካሄደው የተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተመሳሳይ በሁሉም ክልልና ሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች መካሄድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የተከናወኑ የፀጥታ ተግባራትን በአካል ተገኝተው ለመገምገም የመስክ ጉብኝት በየደረጃው እንደሚካሄድ የገለፁት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ክልልና ጣቢያዎች ከማድረስ ጋር በተገናኘ

የፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽኖች በተቀናጀ መልኩ ማከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ከማድረግ አንፃር ፖሊስ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.