Fana: At a Speed of Life!

የፓለቲካ ፓርቲዎች የኘሮግራም ማስተዋወቅና የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር በጎንደር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የብልፅግና፣ እናትና አብን ፓርቲዎች የኘሮግራም ማስተዋወቅና የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብር በጎንደር ከተማ ተካሄደ፡፡
የአማራ ብልፅግና ፖርቲ የአራቱ ጎንደር ዞኖች የምርጫ ቅስቀሳ ማስጀመሪያ መርሃግብር ሲያካሂድ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ፓርቲው መነሻ ያደረገው የህዝብን ፍላጎትና ሃሳብ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የሚያተርፈውም የጋራ ሃሳብና አንድነት እንጂ ብሔርን ብቻ ይዘው አገርን እየተዉ ባለመሆኑ ወደ አንድነት መመለስ ይገባል ብለዋል።
ታሪክን እያዛቡ አገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚፈልጉ አካላትም ይደክማሉ እንጂ አይሳካላቸውምና በብልፅግና ዘመን የቀደመ አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ወደፊት መጓዝ ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ የዘንድሮው ምርጫ በሂደቱም በውጤቱም እንከን የሌለው ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ በጋራ ተረባርበን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በክልሉ የርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ በበኩላቸው የዘንድሮው ምርጫ ካለፉት ጊዜያት የሚለየው የህወሃት ቡድን የፈረሰበት፣ ወቅቱ ፈተና የበዛበት፣ ያለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሜዳ የተዘጋጀበትና በቂ ዝግጅት የተደረገበት መሆኑ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የእናት ፓርቲ የፓለቲካ ኘሮግራሙን የማስተዋወቂያ መድረክ ሲካሄድ ፓርቲው “ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እናት ናት” የሚለው ፓርቲው ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሀገር ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡና መብትና ጥቅማቸው እንዲጠበቅ እሰራለሁ ብሏል።
የእናት ፓርቲ የላዕላይ ምክርቤት አባልና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አቶ ብርሀኑ ፀሀይ ፓርቲው “እኛና እነሱ” የሚል ክፍፍልን ለማስቀረት እንደሚሰራ ገልጸው ኢትዮጵያውያንን ለጋራ አላማና አብሮነት በማሰለፍ “አኩሪ ስልጣኔ ያሳየችው ሀገር ያን የከፍታ ታሪኳን እንድትደግምና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን” ማቀዱን ተናግረዋል።

 

የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም በበኩላቸው ፓርቲው የአማራን ህዝብ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እና ከሌሎች ሀይሎች ጋር በመሆን ደግሞ እኩልነትና ወንድማማችነት የሰፈነባት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ፓርቲው ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ሁለንተናዊ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አቶ የሱፍ አስታውቀዋል።
በ ሙሉጌታ ደሴ፣ ነብዩ ዮሐንስ እና ክብረወሰን ኑሩ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.