Fana: At a Speed of Life!

የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድር መሰረዙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድር መሰረዙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዛሬው እለት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በ2012 ሲካሄዱ በነበሩ አጠቃላይ የሊግ ውድድሮች እጣ ፈንታ ላይ በዛሬው እለት በቴሌ ኮንፈረንስ እና በአካል በፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡ የሊግ ውድድሮች ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ ውይይት ያደረገው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ጋር ዛሬ ደግሞ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አብይ ኮሚቴ ጋር በጉዳዩ ላይ መምከሩን አስታውቋል።

ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ መሆኗን ከግምት በማስገባት እና ወረርሽኙን መቼ መቆጣጠር እንደሚቻል ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ቀጣይ ውድድሮች መቼ እንደሚደረግ ማወቅ ስለማይቻል ውሳኔ ማሳለፉን ገልጿል።

በዚህም መሰረት የ2012 ሁሉም የሊግ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ የተሰረዙ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ውድድሩ በመሰረዙም በየትኛውም ሊግ ሻምፒዮን እንዲሁም ወራጅ የሌለ በመሆኑ ቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን የሚወክል ክለብ አይኖርም ብሏል።

በ2012 ሰኔ 30 ኮንትራታቸው የሚጠናቀቅ ተጫዋቾች ኮንትራት ጊዜያቸው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ክለቦች ኮንትራታቸውን እንዲያከብሩ መወሰኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.