Fana: At a Speed of Life!

የ4 ግለሰቦችን ህይወት ያጠፋው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 2 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከባለቤቱ ጋር በተፈጠረ ጊዜአዊ አለመግባባት የ4 ግለሰቦችን ህይወት መሳሪያ ተኩሶ ያጠፋው የፖሊስ አባል ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪው የግድያ ወንጀሉን የፈፀመው መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ጨርጨር ጊርጊሮስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምዩኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጄላን አብዲ ÷ ረዳት ሳጅን መልህቁ መኪ የተባለው ተጠርጣሪ የፖሊስ አባል ከባለቤቱ ጋር በትዳር ለሁለት አመት አብረው ሲኖሩ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ከ15 ቀን በፊት ባለቤቱ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት መሄዷን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪው የፖሊስ አባልም ከባለቤቱና ከቤተሰቦቿ ጋር የተፈጠረውን አለመግባባት ምክንያት በማድረግ ለስራ የታጠቀውን ክላሽ ኮቭ መሳሪያ ይዞ ወደ ባለቤቱ ቤተሰቦች ቤት በመሄድ የሚስቱን እናት ፣የእንጀራ አባቷን ፣የእህቷን ባል እና የቤት ሰራተኛን በአጠቃላይ 4 ግለሰቦችን ተኩሶ በመምታት ህይወታቸው እንዲያልፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

ግለሰቡ ወዲያውኑ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን÷ የተለያዩ የቴክኒክና የታክቲክ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ ሂደቱ የተጀመረ መሆኑን እና ምርመራውንም በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለሚመለከተው የፍትህ አካል እንደሚላክ ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል።

የአዲስ አመት የበዓል አከባበር በሰላም እንዲከወን መላው የፖሊስ አባላትና የፀጥታ ሃይሉ ሌት ከቀን ሃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት ሲፈፅሙ ብልሹ ስብዕና ባለው አንድ የፖሊስ አባል የተፈፀመው ተግባር ኮሚሽኑን በእጅጉ ያሳዘነ ነው ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ ድርጊቱ የፖሊስ አባላቱን እና የፀጥታ ሃይሉን የማይወክል መሆኑን ገልጸው ÷ ለሟች ቤተሰቦችና ለአካባቢው ማህበረሰብ በኮሚሽኑ ስም መፅናናትን ተመኝተዋል።

ሃላፊው አያይዘውም በማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ሰከን ባለ መንፈስ በመነጋገር በውይይት መፍታት ካልሆንም የተፈጠረው ችግር በህግ አግባብ እንዲፈታ ማድረግ ተገቢ ነው ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.