Fana: At a Speed of Life!

የ65 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ማርገዛቸውን ሳያውቁ ወንድ ልጅ ተገላገሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት 65 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋዋ ወይዘሮ ስንዱ ሰውነት ማርገዛቸውን ሳያውቁ ወንድ ልጅ በምጥ ተገላገሉ።

ወይዘሮዋ በጠላና በአነስተኛ ጉልት አትክልቶችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ናቸው፤ ከብዙ ዓመታት በፊት ባጋጠማቸው ውርጃ ሳቢያ ልጅ ወልደው ለመሳም ሳይታደሉ ዕድሜያቸው መግፋቱን ይናገራሉ።

ልጅ ወልዶ ለመሳም ባለመታደላቸው ፈጣሪያቸው ልጅ እንዲሰጣቸው ሌት ተቀን ሲማፀኑ መኖራቸውንና በኋላም ተስፋ መቁረጣቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ስንዱ ‘የወር አበባ ማየት ካቆምኩኝ ረጅም ጊዜ ተቆጥሯል’ ይላሉ።

ግንቦት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ወይዘሮ ስንዱ ሆዴን አሞኛል፣ ይቆርጠኛል ሲሉ ወደስራቸው ለሄዱት ባለቤታቸው በስልክ ይናገራሉ።

ባለቤታቸው የተለመደ የጨጓራ ህመም እንዳለባቸው የሚያውቁት አባወራ “ፈሳሽ ነገርም አየሁ” ማለታቸው ቢያሰጋቸው ጎረቤቶቻቸው ወደ ጤና ጣቢያ እንዲወስዷቸው ያሳስባሉ።

ጎረቤቶችም ወይዘሮ ስንዱን ገርጂ አካባቢ ወደሚገኘው ድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ይወስዷቸዋል።

ምርመራ ያደረጉላቸው ሐኪሞች ወይዘሮዋ ነፍሰ ጡር እንደሆኑና ህመሙም ምጥ እንደሆነ በማስረዳት ዘጠኝ ወር ሙሉ ለምን የሕክምና ክትትል እንዳላደረጉ ይጠይቃሉ የወይዘሮዋ ምላሽ “ነብሰ ጡር መሆኔን አላውቅም” ነበር።

በዚህ ጊዜ የድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል የላካቸው ወይዘሮ ስንዱ በሆስፒታሉ ማዋለጃ ክፍል ወንድ ልጅ በምጥ ይገላገላሉ።

በአራስ ቤት ወንድ ልጃቸውን የታቀፉት ወይዘሮ ስንዱ ስለ ነብሰጡርነታቸው የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረና በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ በመሆኑ እስከወለዱበት ዕለት ድረስ ከባድ ስራዎችን ይሰሩ እንደነበር ነው የተናገሩት።

ስለ ባለቤታቸው እርግዝና የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ የገለጹት ባለቤታቸው አቶ ሀብታሙ ገላን ሳያስቡት አባት በመሆናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።

የተወለደው ልጅ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝም ልጃቸውን በስስት እየተመለከቱ ነው የተናገሩት።

የእኚህ ሴት ልጅ የማግኘት ጉጉት የጎረቤቶቻቸውን ልጆች እንደራሳቸው ልጆች እንዲንከባከቡ አድርጓቸዋል። ከልጆች ጋር ያላቸው ቅርበትም የልጆቹን ልዩ ፍቅር አስገኝቶላቸዋል፤ ለዚህ ጎረቤቶቻቸውም ምስክሮች ናቸው።

ጎረቤቶቻቸው ወይዘሮ የሺ ጌታቸው እና አቶ ንጉሴ መኮንን ልጅ በጣም ይፈልጉና ይጓጉ ለነበሩት ወይዘሮ ስንዱ ፈጣሪ በመስተመጨረሻ ስለሰጣቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ስንዱ የእርሳቸው የዕድሜ እኩያ መሆናቸውን የገለጹት የ64 ዓመቱ ተስፋ ሊቃውንት ተስፋ መስፍን ደግሞ በዚህ ዕድሜያቸው መውለዳቸውን “የፈጣሪ ድንቅ ስጦታ ነው” ብለውታል።

 

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዘናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

ምንጭ፡- ኢዜአ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.