Fana: At a Speed of Life!

ያልተዘጋጀ አመራር ሀገርና ህዝብን ማገልገል የሚሳነው በመሆኑ አመራሩ የፓርቲውን መመሪያዎችና ፖሊሲዎችን አውቆ ዝግጁ ሊሆን ይገባል- ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና የመዝጊያ ስነ ስርዓት ዛሬ ተከናውኗል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት በተካሄደው በዚህ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው የማጠቃለያ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ስልጠናው አመራሩ እርስ በርስ እንዲተዋወቅ፣ አቅሙን አጎልብቶ ህዝቡን እንዲያገለግል ታሳቢ ተደርጎ መዘጋጀቱን እና ይህም ግቡን መምታቱን አንስተዋል።

ስልጠናው በቂ ባይሆንም ለመጀመር ያህል አመራሩ ራሱን ለተልዕኮ እንዲያዘጋጅ መንገድ የከፈተ ነውም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ያልተዘጋጀ አመራር ሀገርና ህዝብን ማገልገል እንደሚሳነው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አመራሩ የብልፅግና ፓርቲ መመሪያዎችን እና ፖሊሲዎችን አውቆ ሁልጊዜም ዝግጁ እየሆነ ሊሄድ ይገባዋል ነው ያሉት።

“የተሰጣችሁ ቦታ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር የሚቆይ ስላልሆነ ባላችሁ የሀላፊነት ጊዜ ህዝባችሁን አገልግላችሁ እለፉ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የፓርቲው የህዝብ እና የውጭ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ እንዳሉት፥ ለ17 ቀናት በዘለቀው የስልጠና ጊዜ የሀገራዊ ለውጡና እመርታው ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።

በለውጡ የታዩ ተግዳሮቶች፣ ለውጡን ለማስቀጠል የነበሩ አካሄዶች እና በቀጣይ ሊደረጉ በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አመራሩ በቂ የሚባል ስልጠና መውሰዱንም ነው ያመለከቱት።

ለውጡን በማሰቀጠል ላይ ከፍተኛ አመራሩ ከህዝቡ ጎን ሆኖ መምራቱን በማስታወስ አሁንም ይህንን አጠናክሮ የአመራር ቁርጠኝነትን እንዲይዝና እንዲተገብር ስልጠናው ግብዓት እንደሆነው አቶ አወሉ አስታውቀዋል።

በአመራሩ መካከል የአመለካከት እና የአስተሳሰብ አንድነት በማምጣቱ ረገድም ስልጠናው ሌላ ትልቅ ግብዓት መሆኑንም አመላክተዋል።

አቶ አወሉ በተለያዩ መንገዶች በራሱ አካሄድ እየሰራ የነበረውን አመራር ወደ አንድ አምጥቶ በአንድ ዓላማ እንዲቆም በማድረጉ በኩል ስልጠናው ጠቅሞታልም ብለዋል።

በአዳዲስ እና ነባር አመራሮች መካከል የነበረውን የልምድ እና የእውቀት ከፍተት በመሙላት ሁለቱም በፓርቲው ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች እና እሳቤዎች ላይ እኩል እንዲሰለፉና በትኩረት እንዲሰሩ እንዳገዛቸውም ነው የገለፁት።

በፍሬህይወት ሰፊው

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.