Fana: At a Speed of Life!

ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ 11 ሸዶችን ይዞ ስራ ከጀመረ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን ÷አሁን ላይ አምስት ኩባንያዎች በአቮካዶ ዘይት፣ በማር፣ ወተትና ቡና ምርቶች ላይ ተሰማርተው ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ በማስገኘት ላይ ናቸው ተብሏል።
የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መምሩ ሞኬ÷ ፓርኩ ወደ ስራ ከገባ ጀምሮ እስካሁን ከ4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን ገልጸው ገቢው በፓርኩ በሚሰሩ ሁለት የአቮካዶ ዘይት አምራች ኩባንያዎች ከተላኩ ምርቶች የተገኘ መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢንዱስትሪዎችን ከገበሬዎች እና ህብረት ስራ ማህበራት ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር የጥሬ እቃ ግብዓትና የምርት የግብይት ሰንሰለት መፈጠር መቻሉንና በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ሁለት ፋብሪካዎች ጋር በተፈጠረ የገበያ ትስስር ከ135 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ፓርኩ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት እንደሚያደርግ ገልጸው እሴት ተጨምሮባቸው ወደ አገር የሚገቡ የቡና እና የወተት ምርቶችን ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የተሟላ መሰረተ ልማት ያላቸውና 150 ኩባንያዎችን ማስተናገድ የሚችሉ ሼዶች ተዘጋጅተው ባለሃብቶችን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.