Fana: At a Speed of Life!

ደቡብ ሱዳን ከሰሞኑ ለግብጽ የጦር ሰፈር እንድትገነባ ፈቃድ ሰጥታለች በሚል የሚናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 26 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ሱዳን መንግስት ከሰሞኑ ግብጽ በደቡብ ሱዳን የጦር ሰፈር እንድትገነባ ፈቃድ ሰጥቷል በሚል የሚናፈሰው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታወቀ።

የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ጁባ ግብጽ በፓጋክ አካባቢ የጦር ሰፈር ትገነባ ዘንድ ይሁንታ ሰጥታለች በሚል በማህበራዊ ትስስር ገጾች እየተናፈሰ ያለው ወሬ ከእውነት የራቀ እና መሰረተ ቢስ መሆኑን አስታውቋል።

በመግለጫው ምንም አይነት መሬት ለግብጽ ጦር ለመስጠት ስምምነት ላይ አልተደረሰምም ነው ያለው፤ መረጃውን መሰረት የሌለውና መሰረተ ቢስ ሲል አጣጥሎታል።

ኢትዮጵያም ሆነች ግብጽ የደቡብ ሱዳን ወዳጅ መሆናቸውን ያነሳው መግለጫው በተለይም በሃገሪቱ ሰላምን ለማስፈን በተደረገው ጥረት በጋራ ያበረከቱን ሚና ጠቅሷል።

በተለይም ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሃይል ውስጥ በመሆን በአብየ ግዛት ሰላምና ፀጥታ ይሰፍን ዘንድ የተጫወተችውን ሚናም አንስቷል።

“ወሬው የደቡብ ሱዳንን ሰላም በማይፈልጉ ሃይሎች የተነዛ ፕሮፓጋንዳ ነው ያለው መግለጫው፥ ጁባ ከጎረቤት ሃገራትና ከቀጠናው ጋር ያላትን ወዳጅነት አጠናክራ ትቀጥላለች” ብሏል።

ደቡብ ሱዳን ሰላም ወዳድ ሃገር እንደሆነች በማንሳትም የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ከጎረቤት፣ ከቀጠናውና ከመላው ዓለም ጋር በትብብር ትሰራለችም ነው ያለው መግለጫው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.