Fana: At a Speed of Life!

ዱራቢሊስ የተባለው ዓለም አቀፍ ላኪ ድርጅት የኢትዮጵያን አቮካዶ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመረ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዱራቢሊስ የተባለው ዓለም አቀፍ ላኪ ድርጅት በኢትዮጵያ የተመረተን አቮካዶ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታውቋል።

የአቮካዶ የሙከራ ምርቱ ወደ እንግሊዝ፣ አውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ በተሳካ ሁኔታ መድረሱ ተገልጿል።

ድርጅቱ ባለፈው መስከረም እና በያዝነው ጥቅምት ወር ላይ ምርቶችን መላክ ጀምሯል፡፡

በዚህም ከደቡባዊ የባህር ዳር አካባቢ ከሚገኘው ቆጋ ቪሌጅ የግብርና ልማት እና በአካባቢው ከሚገኙ አነስተኛ አምራቾች የተገኙ ትኩስ የአቮካዶ ምርቶች ማቅረቡን ገልጿል።

በዓለም አቀፍ የጥራት ተቆጣጣሪ አካል ፈቃድ የተሰጠው የአቮካዶ ምርት በእንግሊዝ ለሚገኙ ሁለት አስመጪ ድርጅቶች ማስረከቡንም ነው የገለጸው።

በተመሳሳይ በቤልጂየምና ኔዘርላንድስ ለሚገኙ ደንበኞች የአቮካዶ ምርቶችን ያቀረበ ሲሆን ምርቶቹን በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችና በሳዑዲ ዓረቢያ ለማቅረብም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን የድርጅቱ ሀላፊ ኤቨርት ዎልፍራንክ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የግብርና ምርት ዕምቅ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት በአቮካዶ ምርት የተጀመረውን ሂደት ውጤታማነት በማየት በሌሎች የአውሮፓ ገበያ መቅረብ የሚችሉ የግብርና ምርቶችን መላክ እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።

ለዚህም 750 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው የባቡር ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትልቅ አማራጭ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ ምርቶችን ከኢትዮጵያ አንስቶ አውሮፓ ገበያ ለማድረስ 30 ቀናትን የሚፈጅ በመሆኑ በቀጣይ ይህን የጊዜ ቆይታ ወደ 24 ሰዓት ማሳጠር የሚያስችል ዕድል አለም ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ ለምለም አፈሯ፣ ምቹ የአየር ፀባዩ፣ በርካታ የውሃ አቅርቦቷና አንጻራዊ የሰራተኛ ክፍያ አመቺ መሆኑ በግብርናው ዘርፍ መልማት የሚችል ሰፊ አቅም እንዳላትም አስረድተዋል፡፡

ምንጭ፡-www.fpcfreshtalkdaily

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.