Fana: At a Speed of Life!

ዳያስፖራው 80ኛ አመት የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድልና የምስጋና ክብረ በዓል ያካሂዳል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) 80ኛ አመት የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች የድልና የምስጋና ክብረ በአል በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚከበር ተገለጸ።

የአሜሪካ ኢትዮጵያውያን የዜጎች ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ጋር በመተባበር ነው በዓሉን የሚያከብሩት።

የበዓሉ የትኩረት አቅጣጫ በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጭ በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች አስተባብሮ ማክበር እንደሆነ የአዘጋጆች ምክር ቤት ገልጿል።

በዓሉ አዲሱ ትውልድ ጀግኖች አርበኞች ለሃገራቸው የከፈሉትን መከራና ስቃይ እንዳይዘነጋና ታሪክ እንዲማርበት ማበረታታት እንደሆነም ተነግሯል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው፤ “የትውልድ ቀረፃ ለሃገር ግንባታ” በሚል ሃሳብ አዲሱ ትውልድ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ለሀገራቸው የከፈሉት መከራና ስቃይ መዘንጋት እንደሌለበት ጠቅሷል።

በሚዘጋጀው የ80ኛ የጥንታዊ አርበኞች ጀግኖች ክብረ በአል ላይ ወጣቶችን በትጋት ለህብረተሰቡ እንዲሰሩ በመጋበዝ በበአሉ ላይና የአባቶች ገድል ሲዘከር፤ የነገ ታሪክ ሰሪ እንዲሆኑ ለትውልድ ቅብብሎሽ እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ እድሉን መስጠትና ማሳተፍ እንደሆነ ገልጿል።

በቪዲዮ ኮንፈረንስ በሚካሄደው ስነስርዓት ወጣቱን በማስተባበር የሀገር ገፅታ ግንባታ ላይ ትልልቅ የዲጂታል የዲፕሎማሲ ስራ መስራትና ምስጋና ማቅረብ እንደሚከናወን አመልክቷል።

በምስጋናው የፋሽሽት ወረራ አስቆጥቷቸው በአርበኝነት ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ጎን ከቆሙት የውጭ ዜጎች ውስጥ የኢጣሊያንን መንግስት ግፍ በግል ጋዜጣቸው እያጋለጡ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር በመቆም በብእራቸው የተፋለሙትና ትልቅ ዋጋ የከፈሉትን የሰብዓዊ መብት አርበኛ እንግሊዛዊቷ ሲልቪያ ፖንክረስት ይታሰባሉ።

በተጨማሪም በመግለጫው አርበኛ ዘርዓይ ደረስ እንደሚዘከሩ ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.