Fana: At a Speed of Life!

ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ስርዓትን ለማሳለጥ የሚያስችለው ቀጠናዊ የጉምሩክ ትራንዚት ዋስትናን ለመተግበር ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የፈረመችው እና ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ስርዓትን ለማሳለጥ የሚያስችለው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ቀጠናዊ የጉምሩክ ዋስትናን ለመተግበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተገለጸ፡፡
ቀጠናዊ የጉምሩክ ትራንዚት ምንነት እና አተገባበርን በተመለከተ ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች እና የአጋር መስሪያ ቤት ባለሙያዎች ኮሚሽኑ ከኮሜሳ ጋር በመተባበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ የተገኙት የጉምሩክ ኮሚሽን የትራንዚት እና መጋዘን ዳይሬክተር አቶ ወጋየሁ አዳሙ÷ ቀጠናዊ የጉምሩክ ትራንዚት ዋስትና ከዚህ በፊት በየሀገራቱ የሚደረገውን ተደጋጋሚ የዕቃ ዋስትና የሚያስቀር እና እቃዎች በአንድ ዋስትና ብቻ እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል አሰራር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በ13 አባል ሀገራት መካከል የተፈረመው አዲሱ የጉምሩክ ትራንዚት ዋስትና ወጪዎችን የሚቀንስ፣ የትራንዚት ጊዜን የሚያሳጥር፣ የእቃ አወጣጥ ሂደቶችን የሚያፋጥን እና ፈጣን የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
አቶ ወጋየሁ አክለውም አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝድ እና ከጉምሩክ የመረጃ ቋት ጋር የሚተሳሰር በመሆኑ ለጉምሩክ አስተላላፊዎች ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ እንደሚሰጥም አስረድተዋል፡፡
ቀጠናዊ የጉምሩክ ዋስትናን ለመተግበር ከኢንሹራንስ፣ ከባንኮች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ የሆኑ ውይይቶች እና የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ይሰጣሉ ማለታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.