Fana: At a Speed of Life!

ዶናልድ ትራምፕ ሆንግኮንግ ከዋሽንግተን የምታገኘውን ልዩ ተጠቃሚነት እንዲቋረጥ አዘዙ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሆንግኮንግ ከዋሽንግተን የምታገኘውን የልዩ ተጠቃሚነት መብት እንዲቋረጥ አዘዙ።

ትራምፕ በዛሬው እለት ለከተማዋ ከዋሽንግተን በሁሉም መስክ የሚሰጠውን የልዩ ተጠቃሚነት መብት የሚያቋርጥ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ ፈርመዋል።

የአሁኑ እርምጃ ቻይና በሆንግኮንግ እንዲተገበር ካወጣችው አዲስ የደህንነት ህግ ጋር በተያያዘ የተወሰደ ነው ተብሏል።

ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግርም ቻይናን በሆንግኮንግ ነዋሪዎች ላይ በፈጸመችው ድርጊት ተጠያቂ የሚያደርግ ፕሬዚዳንታዊ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላም ሆንግኮንግ በአሜሪካ በኩል ልክ እንደ ቻይና ትታያለችም ነው ያሉት።

በፕሬዚዳንቱ ውሳኔ መሰረትም አሜሪካ ለሆንግኮንግ ልዩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት አትሰጥም አስፈላጊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንም አትልክም።

ትራምፕ ከልዩ ተጠቃሚነቱ ባለፈም ቻይና በሆንግኮንግ ለተገበረችው አዲስ ህግ እገዛ ባደረጉ ባንኮችና ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ የሚጥል ረቂቅም አጽድቀዋል።

ቻይና በበኩሏ የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ የአጸፋ እርምጃ እወስዳለሁ ብላለች።

የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሆንግኮምግ ጉዳይ የቻይና እንጅ የሌላ ሃገር አይደለም ሲል አሜሪካ ጣልቃ አትግባብኝ ብሏል።

ምንጭ ፤ ሬውተርስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.