Fana: At a Speed of Life!

ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን አለመቀበላቸው አሳፋሪ ነው -ጆ ባይደን

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤቱን አለመቀበላቸው አሳፋሪ ነው ሲሉ ጆ ባይደን ገለፁ።

ባለፈው ቅዳሜ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን እንዳሸነፉ የተነገረላቸው ጆ ባይደን፤ ዶናልድ ትራምፕ ውጤቱን ባይቀበሉም ከውጭ ሀገራት መሪዎች ጋር ግንኙነት መጀመራቸው ተነግሯል።

በርካታ ግዙፍ መገናኛ ብዙሃን ጆ ባይድን ማሸነፋቸውን ይፋ ያደረጉ ቢሆንም ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ በማህበራዊ ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።

የምርጫ ቆጠራው አሁን ላይ ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃንም በየአራቱ አመቱ የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ ቀድሞ የመገመት ልምድ አላቸው።

ይህንን ተከትሎም ጆ ባይደን ከዓለም ሀገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ደርሷቸዋል።

ነገር ግን ይህ የምርጫው ውጤት የአሜሪካ የምርጫ ሂደትን በሚመራው አካል ማረጋገጫ ያልተሰጠው ሲሆን የተረጋገጠ ውጤት ይፋ የሚሆነው ከአንድ ወር በኋላ ነው።

ጆ ባይደን ይህ የዶናልድ ትራምፕ አካሄድ የፕሬዚዳንቱን ውርስ አያስቀጥልም ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ይህ ሁሉ ነገር በመጨረሻው ቀን ማለትም ከዶናልድ ትራምፕ ስልጣኑን በሚረከቡበት ዕለት ስኬቱ ይረጋገጣልም ነው ያሉት ጆ ባይደን።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.