Fana: At a Speed of Life!

ዶ/ር ሊያ ታደሰ የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የ2021 ኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማት አሸናፊ ሆኑ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የ2021 ኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማት አሸናፊ ሆኑ።

የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ በበይነ መረብ የተካሄደ ሲሆን የትምህርት ክፍሉ ዲን ሚሼል ኤ. ዊሊያምስ፥ ዶክተር ሊያ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር በወሰዷቸው ወሳኝ እርምጃዎች ለሽልማት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

የትምህርት ቤቱ የኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማት አሸናፊ የሚሆኑት በጠንካራ ራዕያቸው እና ተነሳሽነታቸው በዓለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽን ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ወጣቶች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በተለይ በዚህ የኮቪድ-19 በፈጠረው ውጥረት ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ወጣቶች ከምን ጊዜውም በላይ አስፈላጊ ሆነው እንደተገኙ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

በየትኛውም የዓለም ሀገራት ውስጥ የጤና ዘርፉን መምራት እጅግ ፈታኝ ነው ያሉት ሚሼሌ ኤ. ዊሊያምስ፥ ዶክተር ሊያ በኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትርነትን ከያዙበት ቀን አንስቶ በተለይ በፈታኙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ሥራቸውን በብቃት የተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኮቪድ-19ን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንፃር በመንግሥት እና በግል ባለሃብቶች መካከል፣ በሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች እና በዓለም አቀፍ በጎ አድራጊ ድርጅቶች መካከል እንዲሁም በምሁራን እና በሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል የፈጠሩት አንድነት እና አብሮነት የሚያስደንቅ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የሐርቫርድ ቲ.ኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ለዚህ የከበረ ሽልማት ስለመረጣቸው የተሰማቸውን ክብር ገልጸዋል።

የኔክስት ጄኔሬሽን ሽልማት የሚሰጠው ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች ለሆኑ እና ጤና እንደ ሰብዓዊ መብት እንዲቆጠር እንዲሁም ወጣቶች “ጤና ለሁሉም”ን የዓለም ቀዳሚ ተግባር እንዲያደርጉ በማነሳሳት ረገድ በሳል አመራር የሰጡ እና ቁርጠኝነት ላሳዩ ግለሰቦች መሆኑ ተገልጿል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.