Fana: At a Speed of Life!

ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍና ለማበረታታት የሚያስችል አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የምርምርና ኢኖቬሽን ዘርፍ ዳይሬክተር ጀነራል ሠላምይሁን አደፍርስ እንደገለጹት፥ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገ ነው።

አሁን ላይ ደግሞ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች ኢንተርፕራይዝ መሆን እንዲችሉ ማበረታቻዎችን የያዘ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመው አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው አዋጁ ለመጽደቅ የሚያስችሉ አስፈላጊ ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

አዳዲስ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ዜጎች ለመደገፍ ሚኒስቴሩ እያወዳደረ መሆኑን ጠቁመው ተወዳድረው ያሸነፉ ፈጣሪዎች የገንዘብ፣ የቴክኒክና የሥልጠና ድጋፎችን እያገኙ መሆኑን አብራርተዋል።

የልማት አጋሮች አሸናፊ ለሆኑ ኃሳቦች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉበት ሥርዓት መዘርጋቱንም ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ አዳዲስ የፈጠራ ኃሳብ ያላቸውን ልጆች ከመደገፍ ባሻገር ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ልጆችም የሚወጡበት ሥርዓት እየዘረጋ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.