Fana: At a Speed of Life!

ጀርመን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ሪፎርም ስኬታማነት ድጋፍ ታደርጋለች – በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር

አዲስ አበባ ፣ ጥር 14 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በኢትዮጵያ ከጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ሁር ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸው ወቅት ሃገራት የቆየ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የፓርላሜታዊ ዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፥ በቀጣይ ከጀርመን መንግስትና ሕዝብ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የመንግስት ፍላጎት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ እያደረገ ያለውን ድጋፉና ትብብር በማድነቅ አፈ ጉባዔው አመስግነዋል፡፡

ሃገራቱ የሚከተሉት የፌደራል ስርዓት ባለ ሁለት ምክር ቤቶች በመሆኑ ከጀርመን መንግስት ጋር የፌደራል ስርዓት እንዲጎለብት በጋራ ለመስራት የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሆነ መናገራቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ስቴፈን ሁር በበኩላቸው ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ሀብት እና ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡

በተለይም የሁለቱ ሃገራት የንግድ ትስስር በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመጥቀስ የጀርመን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡

አያይዘውም የጀርመን መንግስት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ሪፎርም የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፥ ለስኬታማነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጀርመን መንግስት የልማት ድጋፍና ትብብር አይለየውም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያና በጀርመን መንግስታት መካከል የቆየ ታሪካዊ እና የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ወደ በላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ነው የገለጹት፡፡

በውይይታቸው የጀርመን መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ ቀጠናዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማትና ዕድገት እንዲኖረው በትብብር ለመስራት ስምምነት ደርሰዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.