Fana: At a Speed of Life!

ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች የሰቆጣ ከተማን ተቆጣጣሩ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 13 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንጸባራቂ ድል ወደፊት እየገሠገሡ የሚገኙት ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች አብዛኞቹን የዋግ ኅምራ አካባቢዎች ነጻ በማውጣት የዞኑን ዋና ከተማ ሰቆጣን ተቆጣጥረዋል፡፡

አካባቢው ከአሸባሪው ሕወሃት ነጻ በሚወጣበት ጊዜ የዋግ ኅምራ ሚሊሻዎች አስደናቂ ጀብዱ የፈጸሙ ሲሆን፥ የአካባቢው ሕዝብም ከመከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመጣመር ደጀንነቱን በብቃት አሳይቷል፡፡

የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች ቀሪዎቹን ሥፍራ እያጸዱ፣ የፈረጠጠውን የአሸባሪውን ጀሌ እየደመሰሱ፣ ወደ አበርገሌ በመገሥገሥ ላይ እንደሚገኙ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በተያያዘም ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች፣ በቆቦ ግንባር በአንድ በኩል ዋጃና ጥሙጋ ላይ የሠፈረውን የጠላት ኃይል በመጥረግ ወደ አላማጣ ከተማ እየገሰገሱ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ተኩለሽን ተቆጣጥረው በማጽዳት ወደ መረዋና ኮረም እየገሠገሡ እንደሚገኙ ነው የገለፀው፡፡

በእሳታማው የጀግኖች ክንድ የተደቆሰው አሸባሪው ሕወሃት፥ ተቸካይና ኋላ ቀር በሆነ የጦር ዘይቤ፣ ዕብሪትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም፣ ከገባባቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች እንደገባ መውጣት አቅቶት፣ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሣራ ደርሶበት ተደመስሷልም ብሏል፡፡

ይሄንን ሐፍረቱን መሸፈን ሲያቅተው በአንድ በኩል ለሰላም ሲል የወጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሽንፈቱ ውኃ የማይቋጥር ምክንያት እያቀረበ፣ አድኑኝ የሚል እሪታ እያሰማ በለመደው ውሸት የትግራይን ሕዝብና የዓለምን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየሞከረ እንደሚገኝ መግለጫው አትቷል፡፡

በዚህ ጦርነት የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የሆነውና አሸባሪውን ሕወሃት በጀግንነት የታገለው የዋግ ኅምራ ሕዝብ፣ በጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ የጸጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም በራሱ በዋግ ኅምራ ሕዝብ ትግል፣ ከአሸባሪው ሕወሃት ነጻ በመውጣቱ፣ በዚሁ አጋጣሚ መንግሥት እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ይወዳል ብሏል በመግለጫው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.