Fana: At a Speed of Life!

ጁንታው ህፃናት ልጆችን ወደ ትምህርት ከመመለስ ይልቅ ወደ ጦርነት አስገድዶ እየማገዳቸው ይገኛል- -ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 17፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ “ጁንታው የትግራይ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በግልፅ እያሳየ ይገኛል ሲሉ በማህበራው ትስስር ገጻቸው በትግርኛ ቋንቋ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ባለፉት ወራት የፌደራሉ መንግስት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካይነት የክልሉ ገበሬዎች እንዳይቸገሩ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ ትራክተሮች እና ሌሎች የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ የተሻለ የእርሻ ሁኔታ ለማመቻቸት ሌት ተቀን ሲሰራ ነበር፡፡ በዚህም ተግባራዊ ዝግጁነት አሳይቷል፡፡
መንግስት ሰብዓዊነትን ያስቀደመ የተናጠል የተኩስ አቁም ሲያውጅ፣ ትኩረት ያደረገው የዝናብ ወቅት ሳያልፍ የክልሉ ገበሬዎች ስራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ እና በክልሉ እየተካሄደ ያለው የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎች እክል እንዳይገጥማቸው በማድረጉ ለህዝቡ ያለውን ታላቅ ክብር አሳይቷል፤ ይሁን እንጂ የህውሃት የጥፋት ሃይል ለራሱ ጥቅም እና ስልጣን የቆመ በመሆኑ እና ለህዝብ የማይጨነቅ በመሆኑ ገበሬዎች የአመት ቀለባቸውን ለማምረት ተረጋግተው እንዳያርሱ በዚህ ወሳኝ ሰዓት ወደ ጦርነት እየማገዳቸው ይገኛል፡፡
በመሆኑም የትግራይ ገበሬዎች ይህን እኩይ የጦርነት ጥሪ ወደ ጎን ትተው ትኩረታቸውን በእርሻ ስራቸው ላይ እንዲያደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡
ህዝብ እንዳይራብ በቂ የእህል ድጋፍ በአስቸኳይ አሰባስበን ወደ ህዝብ እንዲደርስ እንደዚሁም የተደራሽነት ሂደቱን በሚመለከት ከመንግስት በተጨማሪ ሌሎ ባለድርሻ አካላት እንዲሳተፉ እየጠራን፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖ አሰራሮችን በመዘርጋት ያለ እረፍት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ይህ ፀረ ህዝብ የሆነ ሃይል ተመልሶ ወደ ህዝቡ ከተቀላቀለ በኋላ ችግር ላይ የወደቀውን ህዝብ ችግሮች ለመቀነስ ከመስራት ይልቅ ጊዜ የማይሰጠውን ጉዳይ ወደ ጎን በመተው ለተጨማሪ ጥፋትና እንግልት እየዳረገው ይገኛል፡፡
ሌላው ቀርቶ ለወራት በየመጋዘኑ የተከማቸው ድጋፍ ወደ ህዝብ እንዳይደርስ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ተረድቶ ህዝቡ በረሃብ እንዳይጎዳ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊያካሂድ ይገባል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ እድሜያቸው ያልደረሱ ህፃናት ልጆችን ወደ ትምህርት ከመመለስ ይልቅ ወደ ጦርነት አስገድዶ እየማገዳቸው ይገኛል፡፡
ይህ ሰብዓዊነት የጎደለው ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪ ለትውልድ ቀጣይነትም ሆነ ለአለም አቀፍ ህጎች ደንታ የሌለው መሆኑን በግልፅ እያሳዬ ይገኛል፡፡
የፌደራል መንግስቱ ይህ የጥፋት ሃይል ሆን ብሎ ያወደማቸውን እንደ መንገድ፣ ስልክ፣ ባንክ እና መብራት የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ በመጠገን ለክልሉ ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ እና የመንግስት ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱና ህዝቡ አገልግሎት ማግኘት እንዲጀምር በማድረጉ ተጨባጭ ለውጦች እንዲመጡ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ፀረ ህዝብ የሆነ የጥፋት ሃይል ይህን የመሰለውን የህዝብና የመንግስት ጥረት እና ስኬት ወደ ኋላ ለመመለስ በግልጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ጠላት የሆነው ራሱ ጁንታው እንጂ የፌደራል መንግስቱ ወይም ሌሎች አካላት እንዳልሆኑ አሸባሪ ቡድኑ በተግባር እያሳየይገኛል፡፡
ስለሆነም የተጀመሩት የመልሶ ግንባታ ስራዎች እውን እንዲሆኑ፣ ገበሬው ወደ እርሻው ነጋዴውም ወደ ንግዱ ሰራተኛውም ወደ ስራው እንዲመለስ እና ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.