Fana: At a Speed of Life!

ጁንታው በዋሻ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ለማደናገር የሚያደርገው ጥረት አይሳካም- መከላከያ ሰራዊት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ጁንታው በዋሻ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብ ለማደናገር የሚያደርገው ጥረት እንደማይሳካ መከላከያ ሰራዊት ገለፀ።

የአገር መከላከያ ሰራዊትን ስም በማጥፋት ህዝብን ብዥታ ውስጥ ለመክተት የሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃንን በህግ እንደሚጠይቅም አስታውቋል።

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሜጀር ጄኔራል መሐመድ በመግለጫቸው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህወሓት የተባለ ድርጅት መሬት ላይ እንደሌለ አመልክተዋል።

“ጁንታው መቃብር ፈንቅሎ ሊወጣ አይችልም፤ ራሱ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ ጠፍቷል” ብለዋል።

ይሁን እንጂ ተበታትነውና በዋሻ ውስጥ ተደብቀው የሚገኙ የጁንታው ትርፍራፊዎችና ከፍተኛ ተከፋይ አክቲቪስቶቻቸው አሁንም የሐሰት ወሬ እየነዙ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የጁንታው ቃል አቀባይ የነበረው ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በስልክ አስተላለፈው ተብሎ የወጣው መልዕክት የትግራይ ወጣቶችን ለማደናገር የተደረገ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በተጨማሪም መከላከያ ከኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ጋር እየሰራ ነው በሚል አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ያሰራጩት ከእውነት የራቀ መረጃ ነው ብለዋል።

“የተወሰኑት የመከላከያ ተቋማት የባንክ ሂሳባቸውን ወደ ኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አዙረዋል” በሚል የተነዛው ወሬ የተሳሳተና እውነትነት የሌለው ነው በማለት ገልፀዋል።

መከላከያና በስሩ ያሉት የልማት ድርጅቶች የሚጠቀሙት የባንክ አካውንት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነውም ነው ያሉት።

ሰራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነት ከፍተኛ መስዋትነት ከፍሎ አገር እያስቀጠለ ባላበት ጊዜ እንደዚህ አይነት ወሬ የሚነዙ አካላት ዓላማ ጁንታው እያራመደ ያለውን የዘረኝነት ቅስቀሳ ማስፈፀም ነው ይላሉ ሜጄር ጄኔራል መሐመድ።

ምንም የተቀየረም ሆነ የተዘዋወረ አካውንት የለም ያሉት ሜጄር ጄኔራል መሐመድ መረጃው የሀሰት ውንጀላ ነው ብለዋል።

ይህን የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል በማለትም ሰራዊቱን የማይገልጽ ዘገባ በመሆኑ እነዚህን አካላት በህግ እንጠይቃለን ነው ያሉት።

በመጨረሻም የቀሩትን የጁንታ ቡድን አባላት ከተደበቁበት ጉድጓድ ለማውጣት የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ነው ያሉት ሜጀር ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ጁንታውን የማደንና ሰላም የማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.