Fana: At a Speed of Life!

ጁንታው የህወሓት ቡድን በመሰረተ ልማት ላይ ባደረሰው ጉዳት ሃገሪቱ ከአገልግሎት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ አጥታለች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጁንታው የህወሓት ቡድን በፈፀመው የሀገር ክህደት ወንጀል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ከአገልግሎት ሊገኝ የሚገባ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ተቋማቱ እንዲያጡ ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ቡድኑ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊትና የመንግስት ተቋማት ጥበቃ ላይ በነበሩ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ላይ የሀገር ክህደት ወንጀል መፈጸሙን ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡

በዚህም በኢትዮ-ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኘው የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንም ኮሚሽኑ አስታውቋል ።

በዚህ መሰረት በአካባቢው በሚገኙ የኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ጁንታው ባደረሰው ጉዳት ተቋሙ ማግኘት ከሚገባው 1 ቢሊየን 370 ሚሊየን 828 ሺህ 689 ብር ማጣቱን በምርመራ መረጋገጡንም ነው ያስታወቀው።

በተጨማሪም በተቋሙ ላይ ሊደርስ የነበረና ግምቱ ከ39 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ብር የሆነ የበይነ መረብ ጥቃት ማክሸፍ መቻሉንም ጠቅሷል።

በተመሳሳይ በሰሜን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ቡድኑ ባደረሰው ጉዳት ተቋሙ 329 ሚሊየን 167 ሺህ 524 ብር ማጣቱ ተረጋግጧልም ነው ያለው።

በዚሁ ጥቃት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በወልቃይት ንዑስ ጣቢያ፣ በማይጨው ንዑስ ጣቢያ፣ በአላማጣ ንዑስ ጣቢያ እና በአሸጎዳ መቐለ ንዑስ ጣቢያዎች ላይ ውድመት የደረሰ ሲሆን በእነዚህ ንዑስ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የምርመራ ቡድኑ በገንዘብ መጠን አስልቶ ወደ ፊት እንደሚገልጽም ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ቡድኑ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ ባደረሰው ጉዳት 14 ሚሊየን 49 ሺህ 70 ሊትር ነዳጅ ከመቐለ ነዳጅ ዴፖ በህገ-ወጥ መንገድ ተቀድቶ የተወሰደ ሲሆን በዚህም ድርጅቱ ማግኘት የሚገባውን 258 ሚሊየን 190 ሺህ 998 ብር ማጣቱ በምርመራ ተረጋግጧል ብሏል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት ላይ በተፈጸመው ጥቃትም በባህር ዳርና በጎንደር አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የተተኮሰ ሮኬት በመሰረተ-ልማት ላይ 43 ሚሊየን 349 ሺህ 784 ብር የሚገመት ጉዳት ማድረሱንም ገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም በረራ ወደ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ አክሱም፣ መቐለ፣ ሁመራ፣ ደሴ፣ ላሊበላ፣ ሰመራና ሽሬ ባለመደረጉ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 147 ሚሊየን 640 ሺህ 223 ብር ማግኘት ከሚገባው ገቢ ላይ ያጣ ሲሆን ሁለቱ ድርጅቶች በድምሩ190 ሚሊየን 990 ሺህ 8 ብር የሚገመት ገንዝብ ማጣታቸው ታውቋል።

በሌላ በኩል ጁንታው የህወሓት ቡድን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መቐለ ቅርንጫፍ በሚገኘው የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ሰራተኛ የሆኑትን የተለያዩ ግለሰቦች በመጠቀም በወቅቱ የትግራይ ክልል መንግስት የንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ሃላፊ በነበሩት በዶክተር አብርሃም ተከስተ ትእዛዝ ሰጭነት በአንድ ቀን ብቻ በህገወጥ መንገድ 800 ሚሊየን ብር አውጥተው የተወሰዱ መሆኑ በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን ከዚህ ባንክ የወጣው ገንዘብ የት እንደደረሰ ወደፊት ምርመራው ሲጠናቀቅ የሚገለጽ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።

በአጠቃላይ ጁንታው የህወሓት ቡድን በፈፀመው የሀገር ክህደት ወንጀል በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ታላላቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ከአገልግሎት ሊገኝ የሚገባው 2 ቢሊየን 949 ሚሊየን 177 ሺህ 220 ብር ተቋማቱ እንዲያጡ ማድረጉንየኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.