Fana: At a Speed of Life!

ጃፓን በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ አቅርቦት የሚውል 30 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ አደረገች

አዲስ አበባ፡ መስከረም 6 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጃፓን በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ የምግብ አቅርቦት የሚውል 30 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።

ድጋፉ በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ፣ በበርሃ አንበጣ ፣ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እንደሚውል ታውቋል።

በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል በአፋር ፣ አማራ ፣ ኦሮሚያ፣በደቡብ፣ ሲዳማ እና ትግራይ ክልሎች የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በ2020 የሰብዓዊ ምላሽ እቅድ መሰረት ተደራሻ እንደሚሆን ተጠቁሟል።

በጃፓን መንግስት በተደረገው ድጋፍ የአለም ምግብ ፕሮግራም 72 ሺህ 440 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥ ፈፅሞ በመርከብ እና በተሸከርካሪ በማጓጓዝ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት መካዘኖች እንዲገባ ማድረጉን በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ፕሮግራም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ይህም በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በኩል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንደሚሰራጭ ተነግሯል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ እና የአለም ምግብ ፕሮግራም በቪዲዮ ኮንፈረሰ ባካሄዱት ስነ ስርዓት ላይ ድጋፉን ይፋ አድርገዋል።

በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ ስቴቨን ኦማሞ ድጋፉ ለኢትዮጵያ የምግብ ደህንነት በወሳኝ ወቅት ላይ የተገኘ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.