Fana: At a Speed of Life!

ጃፓን ከፉኩሺማ የተበከለ ውሃ ወደ ውቅያኖስ ለመልቀቅ የቀረበውን ዕቅድ አጸደቀች

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 5 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጃፓን ከፉኩሺማ ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ ከ1 ሚሊየን ቶን በላይ የተበከለ ውሃ ወደ ውቅያኖስ ለመልቀቅ የቀረበውን ዕቅድ አጸደቀች፡፡

አሁን ላይ ውሃውን ወደ ውቅያኖስ መልቀቅ የሚያስችለው ዕቅድ የመጀመሪያ ይሁንታ ያገኘ ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ግን አመታት ሊፈጅ ይችላል ተብሏል፡፡

የሃገሪቱ ባለስልጣናትም ከፈረሰው ኒውክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያ የወጣውን ውሃ ወደ ውቅያኖስ የመልቀቁ ሂደት በሁለት አመታት ውስጥ ሊጀመር ይችላል ብለዋል፡፡

ውሃው ከመለቀቁ ቀደም ብሎ ግን አስፈላጊው ማጣራትና ህክምና ይደረግለታልም ነው የተባለው፡፡

ይህም በካይና መርዛማ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድ ውሃውን ለመጠጥና አሳ እርባታ ለመጠቀም እንደሚያስችልም ባለስልጣናቱ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጅ ይህ የጃፓን እቅድ ከበርካቶች ተቃውሞን እያስተናገደ ነው፡፡

የሃገሪቱ አሳ አስጋሪዎች ኢንዱስትሪን ጨምሮ ጎረቤት ሃገራት ዕቅዱ አደገኛ ነው ሲሉ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡

ደቡብ ኮሪያና ቻይናም ቶኪዮ ጉዳዩን ልታስብበት ይገባል ሲሉ ማስጠንቀቂያ አዘል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በአንጻሩ አሜሪካ ዓለም አቀፉን የኒውክሌር ደህንነት መስፈርት ባሟላ መልኩ ጃፓን እቅዷን ተፈጻሚ ማድረግ ትችላለች ስትል አጋርነቷን አሳይታለች፡፡

ተመራማሪዎች ውሃው ከተጣራና አስፈላጊው ህክምና ከተደረገለት በኋላ በሚኖረው የመቀላቀል ሂደት ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ አይኖርም ቢሉም፥ ውሃው ውስጥ የሚቀሩ ንጥረ ነገሮች በመጠን ሲበዙ ብቻ ሰው ላይ ጉዳት እንደሚያስከትሉም መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡

የፉኩሽማ ኒውክሌር ማብላያ ጣቢያ በፈረንጆቹ 2011 የጃፓንን ሰሜናዊ ምስራቅ ክፍል በመታው ርዕደ መሬትና እሱን ተከትሎ በተነሳው ማዕበል ሳቢያ ጉዳት ደርሶበት አገልግሎት አቁሟል፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.