Fana: At a Speed of Life!

ግብረሃይሉ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ተዓማኒ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ተዓማኒና ፍትሃዊ ሆኖ በስኬትእንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማቱ ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ በላኩት መግለጫ÷ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ የህዝባችንንና የሀገራችንን ደህንነት እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅማችንን በማረጋገጥ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ክስተት ስለሆነ መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ከፍ ባለ ጨዋነት እና ስነ ምግባር ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ዳግም ታላቅ ህዝብ መሆናቸውን አስመስክረዋል ብሏል የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማቱ በመግለጫው።

መላው ህዝብ ያሳየው ከፍተኛ ተሳተፎ፣ ቁርጠኝነት፣ ትዕግስትና ትብብር ለምርጫው ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምዱ የውስጥና የውጭ ሃይሎችን አንገት ማስደፋቱንም ገልጿል፡፡

የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት ሀገራዊ ሪፎርሙን ተከትሎ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻና ገለልተኛ ሆነው የህዝብን ሰላምና የሀገርን ደህንነት እንዲያስከብሩ እንዲሁም ብሔራዊ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን እንዲያረጋግጡ የተቀመጠው አቅጣጫና የተሰራው ስራ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍሬ ማፍራቱን መግለጫው ጠቁሟል።

ተቋማቱ ሁሉንም የምርጫው ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች በገለልተኝነት መርህ እኩል በማገልገላቸው የምርጫው ሂደት የጎላ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው እንዲጠናቀቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የምርጫውን ሂደት ከታዘቡ አካላት እንዲሁም ህብረተሰቡ ከሰጣቸው ግብረመልሶች መረጋገጡን አመልክቷል፡፡

6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በስኬት ለማጠናቀቅ ይቻል ዘንድ የፀረ-ሰላምና አሸባሪ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ትርጉም ያለው ተፅእኖ እንዳይኖራቸው በማድረግ ረገድ በቅድመ ዝግጀት ወቅት የተከናወነው ስራ ውጤት አስገኝቷልም ያለው መግለጫው።

በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ደኅንነት ስትራቴጂ ማዘዣ አማካኝነት የሰው ሃይልንና ቴክኖሎጂን በማቀናጀት ከምርጫው ሂደት ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ክስተቶች ዙሪያ ከአንድ ማዕከል ሁለገብ ክትትልና ፈጣን የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱም ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተጨባጭ አቅም መፍጠሩን ጠቁሟል፡፡

ሂደቱ የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማቱ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ተሞክሮ ያገኙበት በመሆኑ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁሟል፡፡

ምርጫው የተረጋጋች ሀገር እውን በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚያበረክት የተገነዘቡት የውጭና የውስጥ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች÷ ሂደቱን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ በመረጃ መረጋገጡን ተከትሎ ጥምረት ፈጥረው የተንቀሳቀሱት የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት የተለያዩ ሴራዎችን ሲያከሽፉ እንደነበር መግለጫው አስታውሷል፡፡

በምርጫውሂደትም የደህንነትና የፀጥታ መዋቅሩ አመራሮችና አባላቱ ለህዝብና ለሀገር ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ሌት ተቀን በመላው ሀገሪቱ በመሰማራት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በሀገር ፍቅር መንፈስ በመወጣታቸው የጎላ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር ጉልህ ሚና ማበርከቱን ጠቅሷል፡፡

ከህዝብ አብራክ ተገኝተው ለህዝብ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ለሀገር ሉዓላዊነት ለከፈሉት መስዋዕትነትም ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት ይገባቸዋል ብሏል፡፡
በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከምንም በላይ ለሀገር ህልውና ቅድሚያ በመስጠት እንዲሁም ለህዝብ ውሳኔ እንደሚገዙ በማረጋገጥ ኢትዮጵያ የተደቀነባትን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተና በጋራ ለመመከት በሚያስችል የአብሮነት መንፈስ የድምጽ መስጠቱ ሂደት እክል እንዳያጋጥመው ያደረጉት ጥረትም ሊደነቅ የሚገባው መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ውጤቱ በይፋ በሚገለጽበት ወቅትም የህዝብን ድምጽ በማክበር ለጋራ ሀገር ግንባታ በትብብር መስራቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ መሆኑን ለማረጋገጥ የተሰማሩ ታዛቢዎች፣ እንዲሁም መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ የተሰማሩ የመገናኛ ብዙሃንና በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት መዋቅር የድምጽ አሰጣጡ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የገለጸው የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት መግለጫ÷ የተጣለባቸውን ግዴታ በላቀ ስነምግባር በመወጣታቸው ምስጋና ሊቸራቸው እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማቱ በየትኛውም ጊዜና ወቅት የሀገራችንን እና የህዝባችንን ፀጥታና ደህንነት የሚጎዱ ከወጭም ይሁን ከውስጥ የሚቃጡ ማናቸውንም ጥቃቶችና ስጋቶች ከመላው ህዝባችን ጋር በመቀናጀት ለመመከት ያለንን የወትሮ ዝግጁነት በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን ብለዋል፡፡

“ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!”
የፌደራልና የክልል የደህንነትና ፀጥታ ተቋማት
ሰኔ 15፣2013ዓ.ም
አዲስ አበባ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.