Fana: At a Speed of Life!

ግድቡን በአንድነት አምረን እና ደምቀን እንደ ጀመርነው፤ እንዳማረብን እና እንደደመቅን እንጨርሰዋለን- ም/ጠሚ አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 26፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ግድቡን በአንድነት አምረን እና ደምቀን እንደ ጀመርነው፤ ፍፃሜውንም እንዳማረብን እና እንደደመቅን እንጨርሰዋለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡
 
ግድቡ ዛሬ የደረሰበት የመጨረሻው የመጀመሪያ ምዕራፍ የትናንት ቁጭታችን መመለስ የጀመረበት ሲሆን፤ ዛሬም የቁጭታችን ጥልቀት እና ከመዳረሻችን ርቀት አንፃር ርብርቡ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል፡፡
 
ግድቡ ተጠናቆ ለጥያቄያዎች መልስ የሚሰጥ፤ ለችግሮች መፍትሄ የሚገልጥ እንዲሁም ለትውልዱ አዲስ ብርሃን የሚፈነጥቅ እንዲሆን አሁንም የህዝባችን ተሳትፎ ወሳኝ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡም ተሳትፎውን ከትላንቱ በላቀ እንደሚገልፅ ሙሉ እምነት አለኝ ነው ያሉት፡፡
 
ለግድቡ ዘላቂ ጤንነት እና የተሳካ የሃይል ምርት በላይኛው ተፋሰስ ሃገራት የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ በተጀመረው ንቅናቄ ግለቱ ዘላቂ እንዲሆን መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
 
የመጨረሻው የግንባታ ፍፃሜ በተሟላ አግባበብ እንዲሳካ በጉልበት፣ በዕውቀት እና በገንዘብ ተሳትፎ ማድረግ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
 
በተያያዘ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የተጀመረው ማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ እና የምርማራ ዘመቻ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።
 
የታላቁ ህዳሴ ግድባችን ከተፋሰሱ ሃገራት ጋር ለምቶ የመልማት መራሂ ዓላማ እንዳለው ድምጻችንን ከፍ አድርገን በኩራት እንናገራለንም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.