Fana: At a Speed of Life!

ግድቡን አስመልክቶ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ገለፀ

አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ80ኛ መደበኛ ጉባኤው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ በነበረው ድርድር ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መክሯል።

ይህንንም ተከትሎ ግድቡን አስመልክቶ ማንኛውም ነገር የኢትዮጵያን ፍላጎትና ጥቅም በሚጠብቅ መልኩ ብቻ እንደሚከናወንና  ብሄራዊ ጥቅሟን የሚነካ ድርድር የኢትዮጵያ መንግስት እንደማያደርግ ነው ያረጋገጠው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ረቂቅ ፖሊሲ ላይም ተወያይቷል።

የቋንቋ ፖሊሲውን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የቋንቋ መብት ህገ-መንግስታዊ እውቅና ቢያገኝም ራሱን የቻለ የቋንቋ ፖሊሲ ስላልነበረ በቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥበቃና ልማት ረገድ የሚነሱ ችግሮች የሚፈቱበት የአሰራር ስርዓትና መርህ ማበጀት በማስፈለጉ መሆኑን ተመልክቷል።

እንደዚሁም የሀገሪቱ ቋንቋ ፖሊሲ መታየት ያለበት ከመብትና እኩልነት አንጻር ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ከምንፈልገው አንድ የጋራ ማህበረሰብ ግንባታና ከምንጋራው ራዕይ ጋር ተቆራኝቶ ጭምር ሊሆን የሚገባው በመሆኑ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ባለድረሻ አካላት ጋር መክሮ ያዘጋጀውን ረቂቅ የቋንቋ ልማትና አጠቃቀም ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

ምክር ቤቱ የአርብቶ አደር ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይም የተወያየ ሲሆን፥ የአርብቶ አደሩን ህዝብ ለየት ያለ አኗኗር፣ የኑሮ መሰረትና ስነ-ምህዳር ከግንዛቤ በማስገባት በየሴክተሩ ተበታትነው ሲተገበሩ የነበሩ የፖሊሲና የስትራቴጂ ወሳኝ ጉዳዮችን ወደ አንድ በማሰባሰብና በማቀናጀት፣ በተደጋጋፊነት ለመስራትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት ሲባል ረቂቅ ፖሊሲው መዘጋጀቱ ተጠቅሷል።

እንዲሁም አገሪቱ አሁን ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ አኳያ በመቃኘት ሁሉም የልማት ሃይሎች ለአርብቶ አደሩ ኑሮ መሻሻል የድርሻቸውን በተጠያቂነት መርህ መወጣት ይችሉ ዘንድ የሰላም ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት የአርብቶ አደር ልማት ረቂቅ ፖሊሲውን አዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ፖሊሲው በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ መሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ65 ነጥብ 3 ሚሊየን ኤስ. ዲ. አር የብድር ስምምነት ነው፡፡

የብድር ስምምነቱ የተደረገው ከአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ጋር ሲሆን፥ አላማውም የአገራችን አርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማህበረሰብ የኑሮ መሰረት እንዲሻሻልና እንዲጠናከር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ትግበራ ለመደገፍ መሆኑ ነው የተመለከተው፡፡

ብድሩም ምንም ዓይነት ወለድ የማይታሰብበት፣ በረጅም አመታት የሚከፈል እና ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ አዋጁ ይጸድቅ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.