Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)ክልሎች ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል።

የደቡብ ክልል መንግስት በመግለጫውም ግድባችንን በልበ ሙሉነት እንደጀመርነው በተባበረ ክንዳችን በላብና በጥረታችን ገንብተን እናጠናቅቃለን ሲል ገልጿል።

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዳር ለማድረስ የሚያስቆመን አንዳችም ምድራዊ ሀይል የለምም ነው ያለው።

የክልላችን ብሎም የሀገራችን ህዝቦች የጋራ ጥረት የግድቡን ግንባታ አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉት ድጋፍ ከፍተኛ ነውም ብሏል።

ህዝባችን የእለት ጉርስ ከሌለው ዜጋ ጀምሮ ሁሉም እንደየ አቅሙ ያለውን እያዋጣ ከዳር እስከ ዳር በአንድ ድምጽ ሆ ብሎ በመነሳት ለግድቡ ግንባታ የድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል።

ይህ ሀገራዊ ፕሮጀክት እውን እንዲሆን የክልላችን ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለምም ብሏል በመግለጫው።

ይህ ህዝባዊ መነቃቃት የፈጠረው ቁጭት ነገ እንደሀገር ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጉዞ የሚያቃልል መሆኑን በመረዳት ነው ብሏል።

ወደ እድገትና ብልጽግና በሚደረግ ጉዞ መቸም ቢሆን የሚገጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናልም ነው ያለው።

ከሚገጥሙን ፈተናዎች ውስጥ የውጭ ጣልቃ ገብነት አንዱ ነው ያለው የክልሉ መንግስት በመግለጫው÷ለዚህም ትራምፕ ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተናገሩት አንዱ ማሳያ ነው ብሏል።

ይህም ንግግራቸው የሀገራችንን ህዝብ ያሳዘነ ተግባር ነው ብለዋል።

ይህንን ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ የክልሉ መንግሥት ሚናውን የሚወጣ ይሆናልም ነው ያለው።

ለዚህም የክልሉ ህዝብ ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚሰነዘረውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በመመከት ረገድ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል ማለታቸውን ከክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመንግስት ወይም የግል ፕሮጀክት ሳይሆን የእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰነዘሩት አስተያየት የግድቡ ባለቤቶች በሆኑት ኢትዮጵያውያን ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚገዳደር በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን አይታገሱም ብለዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ፣ ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያን ያለልዩነት እየገነቡት የሚገኝ የአንድነት መገለጫቸው በመሆኑ፣ ለግድቡ ደህንነትም በጋራ እንደሚቆሙም ነው የተናገሩት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝቦች ከሌሎች የኢትዮጵያ እህት ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው በግድቡ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውንም አቶ አሻድሊ አረጋግጠዋል።

“ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ለሚመጣ ድርድር አያውቁም” ያሉት ርዕሰ-መስተዳር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ ታሪካቸውም ይህንኑ በጉልህ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አባይን ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራ ለመጠቀም እየሠራች መሆኑን አስታውሰው፣ የሚጠቅመው “ከእኔ ብቻ ልጠቀም” እሳቤ ወጥቶ በውይይት ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የበለጠ ማጎልበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት እና ሕዝብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅም ሆነ የግድቡን ደህነነት ለመጠበቅ ሁሌም ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተመሣሣይ ዜናም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ÷ ኢትዮጵያዊያን የውስጥ ችግር ቢኖርም ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ላይ በአንድነት መቆም አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባዋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ÷ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የሰነዘሩት አስተያየት የግድቡ ባለቤቶች በሆኑት ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው አጽኖኦት ሰጥተዋል።

ግድቡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከዕለት ጉርሱ ቀንሶ እየገነባው ያለና የሕልውናው ፕሮጀክት በመሆኑ የራሱን ሀብት ለመጠቀም የማንንም ፈቃድ አይፈልግም ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን በራሳችን ሀብት እንዳንጠቀም በውስጥ ችግሮች ተጠምደን እንድንበጣበጥ ከሚያደርጉ አካላት መንቃት ያለብን ጊዜው አሁን ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።

የቱንም ያህል የውስጥ ችግሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያዊ በብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት ጉዳይ አይደራደርም፤ የቀደመው የአገር ፍቅርና መቆርቆር በዚህ ትውልድም አለ ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ከተነሳን የሚበግረን ኃይል የሌለ በመሆኑ በጋራ መቆም ይገባናል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.