Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ፓርቲዎች 6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተጠናቀቀ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያካሂዱ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ፓርቲዎች 6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተጠናቀቀ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያካሂዱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ አሳለፈ።

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ሂደት በሚያከናውንበት ወቅት የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ዓ.ም. እና በመመሪያ ቁጥር 3 መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ በማድረግ እስከ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ እንዲያቀርቡ የተገለፀላቸው ፓርቲዎች እንደነበሩ አስታውሷል።

ቦርዱ በ2012 ዓ.ም. ሊያካሂድ የነበረው 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ተላልፎ እንደነበር ያስታወሰው ቦርዱ በአሁኑ ወቅት የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ሆኖ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ነገር ግን ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ የተገለፀላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በተጠቀሰው ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ በሚያደርጉት የምርጫ ዝግጅት እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንደሚፈጥርባቸው ገልፀው ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ እንዲፈቀድላቸው ለቦርዱ ጥያቄ ማቅረባቸው ነው የተነገረው፡፡

ቦርዱም ጥር 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ጥር 30 ቀን 1013 ዓ.ም. ድረስ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱ ያሳለፈውን ውሣኔ እንዲራዘምላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ መርምሯል፡፡

በዚህም ቦርዱ የ6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የገባ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ ቢያካሂዱ ጫና የሚፈጠርባቸው መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት 6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተጠናቀቀ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ አካሂደው መተዳደሪያ ደንባቸው ላይ ማስተካከያ በማድረግ እንዲያቀርቡ ወስኗል፡፡

በመሆኑም የምርጫ ተሳትፎ ዝግጅት ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በተጠናቀቀ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በማከናወን ማሻሻያዎቻቸውን ለቦርዱ እንዲያቀርቡ አሳስቧል።

ይህ ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ላይ ብቻ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.