Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤይሩት ከሚገኘው ቆንስላ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቤይሩት ከሚገኘው ቆንስላ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ አሳስበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤይሩት በደረሰው ከፍተኛ ፍንዳታ እና ጉዳት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀዋል።

በሊባኖስ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ቤይሩት-ሊባኖስ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ፅህፈት ቤት ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩ ነው ያሳሰቡት።

ቆንስላ ጄኔራል ፅህፈት ቤቱም በቤይሩት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፍንዳታው ከተከሰተበት አካባቢ ራሳችውን እንዲጠብቁና እንዲርቁ፣ የአገሪቱን የዜና አውታሮች እንዲከታተሉ፣ መረጃዎችን እንዲለዋወጡ አሳስቧል።

በተቻለ መጠን ከመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ እንዲቆዩ ወይም ብዙ እንዳይርቁም ነው ፅህፈት ቤቱ ያሳሰበው።

ትናትና በቤይሩት በተከሰተው ከፍተኛ ፍንዳታ የ100 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 4 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

በከተማዋ ዳርቻ በሚገኝ ወደብ የተከሰተው ፍንዳታ ንዝረት መላ ከተማዋን ማናወጡን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

ፍንዳታውን የተከሰተው በወደቡ አካባቢ ተካማችቶ የነበረ 2 ሺህ 500 ቶን የሚመዝን ኬሚካል ሲሆን ለስድስት ዓመታት ደህንነቱ ሳይጠበቅ ተከማችቶ እንደነበረ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ማይክል አውን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.