Fana: At a Speed of Life!

ብልፅግና ፓርቲ በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለአህጉሪቱ እድገት ከኤ ኤን ሲ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን  ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡብ አፍሪካ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ (ኤ.ኤን.ሲ) 108ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ ተካፈሉ።

ክብረ በዓሉ በኪምበርሊ የተካሄደ ሲሆን፥ የኤ ኤን ሲ እና የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ በብልፅግና ፓርቲ ስም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ኢትዮጵያውያን ለደቡብ አፍሪካውያን የላኩትን ሰላምታ አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት ኤ ኤን ሲ ትውልዶች እየተቀባበሉ የገነቡት ፓርቲ መሆኑን አንስተዋል።

ደቡብ አፍሪካውያን አፓርታይድ እንዲያበቃ ያደረጉትን ትግል ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜ እንደሚያደንቁም ነው የተናገሩት።

በኤ ኤን ሲ አመራርም ደቡብ አፍሪካ የበለጠ እኩልነት የሰፈነባት እና የበለፀገች ሀገር እንደምትሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ ግንኙት ከበርካታ አስርት ዓመታት በፊት በዲፕልማሲያዊ ግኑኝነት መጀመሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ሁለቱ ሀገራት ህዝቦች የጋራ በሚያደርጓቸው ታሪኮች የተሳሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ እንደ ሀገራቸው እየኖሩ መሆኑን በማንሳት፤ ደቡብ አፍሪካ ለዚህ እንግዳ ተቀባይነቷ እና ለኢትዮጵያውያን በራፏን በመክፈቷ እናመሰግናለን ነው ያሉት።

የነፃነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በማንሳት እና ስለ ኢትዮጵያ የተናገሯቸውን በማስታወስ ኢትዮጵያ ዛሬም ማንዴላ ለታገሉለት ነፃነት እና ሰብዓዊነት እንደምትቆም ተናግርዋል።

በንግግራቸው ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ የቆዩበትን ስፍራ ታሪካዊነቱ ተጠብቆ ሁለቱ ሀገራት በጋራ እንዲያለሙት ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ፓርቲያቸው ብልፅግና ፓርቲ በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ብሎም ለአህጉሪቱ ብልፅግና ከኤ ኤን ሲ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ግብዣ ነው በሀገሪቱ የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ በመሪዎች ደረጃ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች የደቡብ አፍሪካ መንግስት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ጥረት ያደርጋሉም ነው የተባለው።

በተጨማሪም በነገው እለት በጆሃንስበርግ በስቴዲየም ከህዝቡ ጋር እንዲገናኙ ዝግጅት ተደርጓል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.